ኢንጅነር ታከለ ኡማ የመስቀል በአል ዝግጅት ላይ ያደረጉት ንግግር

የመስቀል በዓል የኢትዮጵያውያንን አንድነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው- ኢንጅነር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመስቀል በዓል የኢትዮጵያን አንድነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለፁ።

ምክትል ከንቲባው የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሲከበር መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህ ወቅት የመስቀልን በዓል አባቶች ፍቅርን፣ ሰላምንና ይቅርታን የሚያውቅ፣ በእርሱም የሚመራ ማኅበረሰብ ለመፍጠርና መደመርን ለማስተማር እንድናከበር አድርገዋል ነው ያሉት።

እንዲሁም እንደ ችቦውና እንደ ደመራው አንድ ሆነን ተባብረን ችግሮቻችንን ካላሸነፍን፣ ሀገራችንንም ካልገነባናት የትም እንደማንደርስ ሊያስተምሩን ነው ብለዋል።

መስቀል የፍቅር፣ የይቅርታና የሰላም ምልክት ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፥ ይህን ታላቅ በዓል ሲከበር ይህንን መልእክት በማንገብ መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምክትል ከንቲባው በንግግራቸው ፍቅር አንድ አድርጎ የሚይዘው ገመድ ነው ሰላም ደግሞ ጥላቻንና ጠብን የሚከላከል መሣሪያው ነው በማለት የገለፁ ሲሆን፥ ይቅርታና መደማመጥ ደግሞ ችግርን መፍታት የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዓሉ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የጎጠኝነትእና የበደል ምንቸቶች ወጥተው የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የእኩልነት ምንቸቶች የሚገቡበት እንዲሆን የአባቶች ፀሎት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የፍቅርና የመደመር በዓል የሆነው የደመራ በዓል ከሀይማኖታዊና ባህላዊ መለያው ባሻገር የኢትዮጵያን ገፅታ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገነባ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

እንዲሁም በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ትፈርሳላች ብለው እንደሚያስቧት ሳትሆን እንደደመራው ችቦ የተገመደች ታላቅ ሀገር እንደሆነችም ገልፀዋል።

እንዲሁም የረዥም ዘመናት ሃይማኖታዊ ትምህርት፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ ወግና ሥርዓት ያለን እንዲሁም ታላቅና ብርቱ ሕዝብ መሆናችንን የሚያሳይ በዓል ነው ብለዋል።

በኤፍሬም ምትኩ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.