ለኦነግ የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ

ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው፤ አሁንም ቢሆን የቀረውን ትጥቅ መፍታት አለበት አለ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት።
===========================================

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ከሰሞኑ የኦነግ አመራር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከአንድ የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከመንግስት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተደራደርንም፤ ትጥቅ የሚፈታም የሚያስፈታም የለም ማለታቸውን ተከትሎ በዛሬው እለት መግለጫ የሰጡት።

አቶ ካሳሁን በመግለጫቸው፥ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ባደረገው የሰላም ጥሪ መሰረት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሀይሎች ወደሀገር መግባታቸውን አስታውሰዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአስመራ በተደረጉ ሶስት ድርድሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ገብቶ ለመፎካከር መስማማቱም አስታውሰዋል። ሆኖም ግን በድርድሩ ወቅት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ እንዳልተነሳ እና ጉዳዩ ያልተነሳውም የመደራደሪያ ጉዳይ ስላልሆነ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ኦነግ ወደ ሀገር ሲገባ 1 ሺህ 300 ያህል ጦሩን ትጥቅ አስፈትቶ መግባቱንና ጦሩም በአሁኑ ሰዓት በጦላይ ማሰልጠኛ ስልጠና እየተከታተለ ነው ብለዋል።

አቶ ካሳሁን አክለውም፥ ሰላማዊ ትግል የሚደረገው በሀሳብ እንጅ በአፈሙዝ ስላልሆነ ትጥቅ የመፍታትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበውና ቀይ መስመር ነው ሲሉ አቶ ካሳሁን በመግለጫቻቸው ተናግረዋል።

ስለሆነም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አቋሙን እንደገና በመፈተሽ ትጥቁን እንዲፈታ መንግስት ጥሪውና ያቀርባልም ብለዋል አቶ ካሳሁን። ይህ ካልሆነ ግን የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገ መንግስታዊ ስርዐቱን ለማስጠበቅ ሲል መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

መንግስት ህግን የማስከበር ስራውን በቆራጥነት ስለሚሰራ መላው ህዝብ የደህንነት ችግር ይገጥመኛል በማለት ስጋት ላይ እንዳይወድቅና እንዳይደናገር መልእክት ማስተላለፋቸውን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.