አስቸኳይ መልዕክት ለኦነግ

በመጀመሪያ ከብዙ ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ከሚወዱትና ከታገሉለት የኦሮሞ ህዝብ መሀል ለመገኘት በመብቃትዎ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ። እርስዎ ወደ ሀገር ቤት በተመለሱበት እለት በፊንፊኔው የአብዮት አደባባይ በአካል ተገኝቼ አቀባባል ካደረጉልዎት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች መካከል አንዱ በመሆኔም ልባዊ ኩራት ይሰማኛል። ከውጪ ሀገር ከተመለሱት የፖለቲካ ፓርቲና የነፃነት ንቅናቄ መሪዎች መካከል በአካል ተገኝቼ አቀባበል ያደረግኩት ለእርስዎ ብቻ ነበር። ይህም ምክንያት አለው።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለመጀመሪያ ጊዜ እና ለረጅም አመታት ከልቤ የደገፍኩት ድርጅት ነው። የግንባሩ ታሪክም ከቤተሰቤ ታሪክ ጋር በጣም የተሳሰረ ነው። እኔ አፈንዲ ሙተቂ የገለምሶ ከተማ ተወላጅ ኦሮሞ ነኝ። እኔን የወለደኝ አቶ ሙተቂ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ፣ አያቴ ሼኽ ሙሐመድ ረሺድ ቢላል እና አጎቴ አሕመድ ተቂ ሼኽ ሙሐመድ (ሁንዴ) ግንባሩ ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ባደረገው ትግል ውስጥ የየራሳቸው ሚና ነበራቸው። የግንባሩ የመጀመሪያ ተዋጊ ኃይል መሥራቾች የነበሩት ኤሌሞ ቂልጡ፣ ሁንዴ ኢቱ (አሕመድ ተቂ)፣ እና ጄኔራል ታደሰ ብሩ ሠራዊቱ እንቅስቃሴውን በሚያደርግበት መንገድ ዙሪያ በየጊዜው ይወያዩ ከነበሩባቸው ስፍራዎች አንዱ እኔ የተወለድኩበት ቤት ነው። መስከረም 5/1974 በጢሮ በተካሄደው ውጊያ አጎቴ አሕመድ ተቂ (ሁንዴ) እና ኤሌሞ ቂልጡ ሲሰውም ሆነ ከዚያ በኋላ በኦነግ ሳቢያ ከፍተኛ እመቃ፣ አፈና፣ ጭቆና፣ አፈና፣ ዘረፋ፣ ክትትል፣ ፍተሻ፣ ማስፈራሪያ ይካሄድባቸው ከነበሩት ቤተሰቦች አንዱ የኔ ቤተሰብ ነው።

የቤተሰቤን ታሪክ የመዘዝኩት ለመታበይና ለግብዝነት አይደለም። ከኛ በላይ ግድያ፣ እስራት፣ ፍዳ፣ መከራና ስቃይ የተቀበሉ ሌሎች የኦሮሞ ቤተሰቦች እንዳሉ አውቃለሁ። የራሴን ቤተሰብ ታሪክ የመዘዝኩት በትግሉ ቀዳሚ ዘመን ከነበረው ተሳትፎ አንፃር ማንነቴን በቀላሉ ተረድተው ለምጠይቅዎት ጥያቄ ቀና ምላሽ ይሰጡኛል በሚል እምነት ነው።
—-
በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት የቀድሞውን አፋኝ ወያኔያዊ አገዛዝ ካስወገደ በኋላ በትጥቅ ትግል የተሰማሩ ድርጅቶች መሪዎች ወደ ሀገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በዚያ ወቅት ኦነግ ወደ ሰላማዊው የፖለቲካ ሽግግር እንዲመጣ ደጋግመው ሲወተውቱ ከነበሩት አንዱ እኔ ነኝ። ይህንንም ያደረግኩት ኦነግ በሽግግሩ ዘመን እና ከዚያ በኋላ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ስለማውቅ ነው። በመሆኑም ኦነግ በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር በመሳተፍ ያለውን እምቅ ክህሎት፣ የአመራር ጥበብ እና የበርካታ ዓመታት የፖለቲካ ልምድ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲያውለው በመመኘት ጥሪዬን ሳቀርብ ቆይቻለሁ።

በእርግጥም የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት የተጠማውንና የታገለለትን ነፃነት፣ እኩልነት ዲሞክራሲ፣ ሰላም እና ልማት እንዲቀዳጅ ለማድረግ የሚቻለው ኦነግን የመሳሰሉት በህዝብ ዘንድ ክብር፣ መልካም ስም እና ተቀባይነት ያላቸው ድርጅቶች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ነው።

ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ ከኦሮሞ ህዝብ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ በነሐሴ እና መስከረም 2018 (ነሐሴ 2010) ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ተመልሷል። በዚህም መላ የኦሮሞ ህዝብ፣ የኦሮሞ ትግል ወዳጆች፣ ጭቁን ህዝቦችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶአቸዋል።

ኦነግ ወደ ሰላማዊ ትግል ከገባ በኋላ ባከናወናቸው ተግባራትም ብዙዎች ተነቃቅተዋል። በተለይም ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ጋር ወደ ውህደት ለማምራት ያሳየው ተነሳሽነት ከኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነበር። ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀጣዩ ምርጫ ገዠውን ፓርቲ መፈተን የሚችሉት ሀይላቸውን አንድ ላይ ሲያሰባስቡ ነውና።
—–
ሰሞኑን ከእርስዎ አንደበት የሰማናቸው ወሬዎች ግን በጣም ረብሸውናል። “ኦነግ በትጥቅ አመጽ ያስመዘገበውን አኩሪ ታሪክ በዲሞክራሲያዊ ሰርዓት ግንባታው ውስጥ በሚያደርገው ተሳትፎም ይደግመዋል” የሚለውን ተስፋችንንም ያደበዘዘ ሆኗል።

በተለይም እርስዎ ከትጥቅ መፍታትና አለመፍታት አንፃር የተናገሩት አረፍተ ነገር ከድርጅትዎ ተቃዋሚዎች አልፎ መላውን ዜጎች በስጋት ውስጥ የጣለ ሆኗል። “ይህቺ ሀገር ከጦርነት አዙሪት ወጥታ ወደ ዲሞክራሲና ልማት የምትመለስበት ጊዜ እየራቀ መሄዱ ነው” የሚል ጥያቄም ቀስቅሷል። ከዚህ አልፎም ነጋ ጠባ የኦነግን ስም ለማጥፋት የሚፈልጉ ሃይሎች የእርስዎን ንግግር እያባዙት “ግንባሩ ከፋሽስታዊ አመራሩ የማይላቀቅ የኋላቀሮች ስብስብ ነው” የሚል ፕሮፓጋንዳ መንዛትም ጀምረዋል።

በእኛ በኩል ኦነግ ከመንግስት ጋር የተደራደረባቸውንና የተስማማባቸውን ነጥቦች በትክክል አናውቅም። ሆኖም እርስዎ የኦነግ ጦር ትጥቁን አይፈታም ያሉበትን መነሻ እንረዳለን። በሽግግሩ ዘመን ወያኔ ሸምጋዮች ባሉበት መድረክ ላይ ባደረገው ስምምነት የኦነግ ጦር ወደ ካምፕ እንዲገባ ካደረገ በኋላ ስምምነቱን ጥሶ በኦነግ ጦር ላይ ከፍተኛ ዘመቻ መክፈቱን በቁጭት እናስታውሳለን።

ከዚያ አንፃር ሲታይ የኦነግ ጦር ትጥቁን እንደማይፈታ መናገርዎ ሊያስኬድ ይችላል። ነገር ግን አሁን ያለንበትን ወቅት ከ1992 የተለየ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። በእኔ እምነት ስለትጥቅ መፍታት የተናገሩት ነገር የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከደረሰበት ደረጃ፣ አዲሱ መንግስት ከመጣበት ሁኔታና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን ካሳየው ቁርጠኝነት፣ የኦሮሞ ህዝብና ሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ለመንግስቱ ከሰጡት አመኔታ፣ በአሁኑ ወቅት ካለው የዓለም አቀፍ ኃይሎች አሰላለፍ፣ የውጪ መንግሥታትና የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ለመንግሥቱ ከሰጡት ድጋፍ ወዘተ ጋር የሚጣጣም አይደለም። የአሁኑ መንግስት “ኦነግን ትጥቅ አስፈትቼው እንደ ከዚህ ቀደሙ ድራማ እሰራበታለሁ” ቢል ማንም ሰው በዝምታ አይመለከተውም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም እንደ በፊቱ በቸልተኝነት አያልፈውም።

ከዚህ ይልቅ የሚያነጋግረው ጉዳይ “የኦነግ ጦር እጣ ፈንታ ምን ይሁን? ትጥቁን ፈትቶ ይበተን ወይንስ ሌላ ኃላፊነት ይሰጠው?” የሚለው ጥያቄ ይመስለኛል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሌሎች ሀገራትን ተመክሮ ማሰስ ያስፈልጋል። በብዙዎች ዘንድ እየተንሸራሸረ ያለው ሐሳብ ግን “ጦሩ ልምድ ያለው በመሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፀጥታ ሃይል አካል ይሁን” የሚል ነው። በዚህ ዘዴም አሁን የተፈጠረውን ውዝግብ በቀላሉ መፍታት የሚቻል ይመስለኛል።

ስለሆነም ከእኔ እና ከበርካታ ኦሮሞዎች እየተሰጡ ያሉ ሐሳቦችን ተቀብለው ከመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመቀራረብ ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ጥሪዬን በአክብሮት አቀርባለሁ። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግስት ኃላፊዎችም ከእርስዎ ጋር ተቀራርበው ችግሩን በውይይት እንዲፈቱት በዚህ ደብዳቤ ግልባጭ አሳውቃቸዋለሁ። በሶሻል ሚዲያ ላይ በተለያዩ ጎራዎች ተከፋፍለው በጉዳዩ ዙሪያ የሚወዛገቡ ቡድኖችና ግለሰቦችም ከዚህ ድርጊታቸው ተቆጥበው ችግሩ በሚፈታበት መንገድ ላይ ብቻ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ እጠይቃለሁ።

አፈንዲ ሙተቂ
አዳማ፣ ምሥራቅ ሸዋ
መስከረም 28/2011 (October 8/2018)

ግልባጭ
ለአቶ አዲሱ አረጋ
ለአቶ ታዬ ደንደኣ
ለአቶ ሚልኪሳ ሚደጋ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.