ኦነግ ትጥቅ ካልፈታ ምን ይከሰታል?

ባሳለፍነው ዓመት ማገባደጃ በወርሃ ነሐሴ አጥቢያ ከበርካታ ጋዜጠኞች ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰየሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ከሁለት ሰዓት በላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በወቅቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል መንግስት የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት ወደ አገር የሚገቡ የታጠቁ ሃይሎችን ይመለከታል፡፡ ጥያቄውም ‹‹የታጠቁ ሃይሎች ከነትጥቃቸው ይቆያሉ ወይ? መንግስትስ ምን አስቧል?›› የሚል ነበር፡፡

በመልሳቸው ‹‹ከነትጥቃቸው የሚቆዩ ከሆነ ለምን ይመጣሉ?›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የለውጡ መርህ ትጥቅ አያስፈልግም የሚል በመሆኑ ሁሉም ሃይል መታጠቅ ያለበት ሃሳብ እና መፅሐፍ ብቻ ነው፡፡ አያይዘውም፤ በክላሽ ከሆነ የሚመጡት መምጣቱ ዋጋ የለውም ሲሉ ደምድመዋል፡፡ ምክንያቱም ትጥቅ እና ሰላም አብረው የማይሄዱ ሁለት ጉዳዮች ናቸው፡፡

በመሆኑም ከሁሉም የታጠቁ ሃይሎች ጋር የተካሄደው ንግግር ትጥቃችሁን ፈታችሁ በሰላማዊ መንገድ በሃሳብ ብቻ ታገሉ የሚል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ከተናገሩ ከወር በኋላ አዲስ አበባ የገባው የኦሮሞ ነፃነት ግምባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በአደረጉት ቃለ ምልልስ ድርጅታቸው ወደ አገር ሲገባ ትጥቅ የመፍታት ዕቅድ አለመያዙን ገልጸዋል፡፡ አሁንም እንደማይፈቱ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከመንግስት ጋር የተደረገ ድርድር የለም ማለታቸውም ይታወሳል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር ምላሽ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው፤ ኦነግ ለገለልተኛና ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሩን ክፍት በማድረግ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤን በመንግስት ስም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ይሄም በዋናነት ለድርጅቱም ሆነ ለአገሪቱ ሕዝቦች ሰላምና ደህንነት ሲባል የተገኘው የሰላም አየር መደፍረስ እንደሌለበት በማመን ነው፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ አገሪቱ ወደ ኋላ የቁልቁለት መንገድ መሄድ የለባትም፤ አይገባትም›› ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ኦነግ ውሳኔውን በማጤን ትጥቁን መፍታት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን መንግስት የመንግስትነት ሚናውን መወጣት ስለሚገባው እና የሕዝቡን ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ስላለበት የፌዴራል የፀጥታ ሃይሎች ትጥቅ የማስፈታት ስራ ያከናውናል ብለዋል፡፡

የኦነግ ሊቀመንበርን መግለጫ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አካላትም የድርጅቱ ፍላጎት በሕግ ሳይቀር ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለሚካኤል፤ እንኳን አይደለም የተደራጀ ሃይል ማንኛውም ግለሰብ ትጥቅ ለመያዝ የመንግስት ፈቃድ ያስፈልገዋል፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን በአገሪቱ ሕግ ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ ከእስር ቅጣት እስከ መሳሪያ መውረስ እርምጃ ያስወስዳል፡፡

‹‹በሕገ-መንግሥቱ እንደተቀመጠው የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት የሚወድቀው በፌዴራል እና በክልል መንግስት ላይ ነው›› የሚሉት አቶ ደበበ፤ በዚህ መሰረት በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የታጠቁ ኃይሎች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ የወንጀል ሕግ እስካልተሻረ ድረስ ኦነግ ትጥቁን ላለመፍታት ምንም አይነት መከራከሪያ ሊያስቀምጥ አይችልም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየውም በትጥቅ ትግል የቆዩ ኃይሎች ወደ አገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ሲወስኑ የመጀመሪያ ተግባራቸው ትጥቅ መፍታት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ይሁንና የትጥቅ መፍታት አለመፍታቱ ጉዳይ በተለየ የፖለቲካ ውሳኔ ተደርሶበት ከነትጥቃቸው እንዲገቡ ቢደረግ እንኳን የታጠቀው ሃይል መቆየት ያለበት በካምፕ ነው፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን ሰራዊቱ ባለበት አካባቢ የፀጥታ ችግር ቢያጋጥም ተጠያቂ ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ሰራዊቱ ምን ያህል መሳሪያ እና ምን አይነት መሳሪያ እንደታጠቀ በግልፅ መረዳት የሚቻለው ካምፕ በማስገባት ነው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን፤ በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ውስጥ ከገባው የኦነግ ሰራዊት ውስጥ አንድ ሺ300 የሚሆን ሰራዊት ብቻ ትጥቅ አስፈትቶ በአርዳይታ በመንግስት ስር ሆኖ የተሃድሶ ስልጠና በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ይሄ ብቻ በቂ ባለመሆኑ በተለይ በኦሮሚያ አጎራባች ክልሎች አካባቢ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቅ ማስፈታት ይገባል፡፡

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ፤ ከመንግስት ጋር ስለ ትጥቅ መፍታት አልተደራደርንም ያሉትን በተመለከተ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ‹‹በመሰረታዊነት ትክክል አይደለም›› ይላሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መንግስት በትጥቅ ትግል አማራጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ የፈለገን ሃይል ወደ አገር አስገብቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግስት እንዲኖር አይፈቅድም፡፡ ጉዳዩም ቀይ መስመር የሚበጅለት ነው፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ፤ የሰላም ጥሪ እየተደረገ ‹‹ትጥቅ አልፈታም›› ማለት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብሎ መንግስት ከድርጅቱ ጋር በትጥቅ መፍታት ዙሪያ ተገቢውን ድርድር ቢደርግ ኖሮ ኦነግ ዛሬ ላይ ‹‹አልተደራደርኩበትም›› የሚል ሰበብ እንዳያስቀምጥ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡

የኦነግ ሌላው መከራከሪያው የታጠቀ ኃይል ‹‹ትጥቅ ፍታ›› ሊለኝ አይችልም የሚል ነው፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ እንደሚሉት ይሄ የድርጅቱ አገላለጽ በራሱ ወንጀል ነው፡፡ ምክንያቱም ትጥቅ የሚስፈታው አካል ትጥቅ ፍታ ከተባለው ሃይል ጋር አብሮ ወደ አገር የገባና በአደረጃጀትም እኩል የሆነ አካል ሳይሆን ትጥቅ አስፈቺው አገር በመምራት ላይ የሚገኘው የአገሪቱ መንግስት ነው፡፡ በሕዝብ የተመረጠና ሕግና ስርዓትን ለማስከበር ሃላፊነት ያለበት በሕግ የተቋቋመን መንግስት በአደባባይ ‹‹ትጥቅ ፍታ ሊለኝ አይችልም›› ማለት በራሱ ወንጀል ነው፡፡

አቶ ካሳሁን፤ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ግንባታና ዴሞክራሲ ዙሪያ የጀመሩትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጡም ወደኋላ አይቀለበስም፡፡ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ ኦነግ የያዘው አቋም ‹‹ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው›› የሚለውን መሰረታዊ የሕግ መርህ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የፖለቲካ ለውጥ የሚገዳደር ነው፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር ከዓለም ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቅ አለመፍታት ችግሩን ማባባስ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የመንግስት እርምጃ መፍጠን ይገባዋል፡፡

ብሩክ በርሄ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.