በኤርፖርት አጭበርብረው ሊያልፉ ሲሉ ተያዙ

ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ህገ ወጥ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአለም አቀፍ ተቋማት ስም ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ህገ ወጥ እቃዎች በቁጥጥር ስር ማዋላቸዉን የቦሌ አለምአቀፍ ኤርፖርት ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በቦሌ አለምአቀፍ ኤርፖርት የጉምሩክ ህግ አስተባበሪ አቶ ምህረተአብ ገ/መድህን ለኢቢሲ እንደተናገሩት ባሳለፍነው ሳምንት በሁለት ኢምባሲዎችና በአንድ አለም አቀፍ ተቋም ስም ሊገቡ የነበሩ ግምታቸው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የመኪና መለዋወጫዎች፣ የሞባይል አክሰሰሪዎች እንዲሁም ወደ ሀገር እንዳይገቡ በመንግስት እገዳና ክልከላ የተደረገባቸው እቃዎች ተይዘዋል፡፡

ዕቃዎቹ ሊያዙ የቻሉት ተጠርጣሪዎቹ የኢምባሲውን ያለመፈተሽ መብት በመጠቀም እቃዎቹን ካስመጡ በኋላ ወደ ኢምባሲው መውሰድ ሲገባቸው ወደ ግለሰብ ቤት በመውሰድ ሊያራግፉ ሲሉ በተደረገባቸው ክትትልና ቁጥጥር መሆኑን አቶ ምህረተአብ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ እቃው ለኢምባሲ የመጣ በመሆኑ መፈተሸ የለበትም ብለው ቢከራከሩም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጨባጭ መረጃ ካገኘ እቃዎቹን የመፈተሸ መብት ስላለው እቃዎቹን ወደ ቦሌ ኤርፖርት ቅ/ፅ/ቤት እንዲመለሱ በማድረግ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢንባሲው እና ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተወጣጡ ተወካዮች በተገኙበት ፍተሻ ተደርጓል፡፡

በተደረገው ፍተሻም ኢምባሲው ለሚኒስቴር መ/ቤቱ በሰነድ ካሳወቀው እቃ በላይና ፍቃድ ያልተሰጣቸው ዕቃዎች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡

እቃዎቹ ወደ ገበያ ቢገቡ ኖሮ በህጋዊ ነጋዴው ላይ ጫና እንደሚያደርሱና የሀገራችንንም ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ወንጀሉም ከባድ የማጭበርበር ወንጀል በመሆኑ ተጠርጣሪዎች ህግ እንዲጠየቁ መ/ቤቱ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመሀመድ ፊጣሞ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.