ወ/ሮ ኬሪያ ከህውሃት አስተሳሰብ የወጣ አስገራሚ ንግግር አርገዋል

ትውልዱ ብሔርን መሰረት አድርጎ መፈራረጅና መጠላላትን እንዳይወርስ ሁሉም ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል – የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

ትውልዱ ብሔርን መሰረት አድርጎ መፈራረጅና መጠላላትን እንዳይወርስ መጠንቀቅ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም አሳሰቡ።

አፈ ጉባዔዋ ይህን ያሉት ዛሬ በምስራቅ ኢትዮጵያ ያሉ ክልሎች የተሳተፉበት በድሬደዋ እየተካሄደ ባለ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ ነው።

ለሁለት ቀናት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በኮንፍረንሱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉትም በአገሪቷ ”የእከሌ ብሔር ካንተ በላይ ተጠቃሚ ሆኗል፣ የእከሌ ብሔር የበላይ ሊሆንብህ ነው” የሚሉ ጥላቻ ሰባኪና ጥርጣሬን የሚዘሩ ቃላት ሥር እየሰደዱ ነው።

በዚህ ምክንያትም በብሔር መፈራረጅና ጥላቻ እየሰፋ መጥተዋል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት በርካቶች በአሰቃቂ መንገድ እየተገደሉ፣ በርካቶች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ፣ ለፍተው ያካበቱትን ጥሪት እያጡ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህን የጥላቻ ትርክት ቆም ብለን አስበን በሰላማዊ አብሮነትና አንድነት ካልቀየርን “በዘር ጥላቻ የተመረዘ ትውልድ መፍጠራችን አይቀርም” ብለዋል።

በብሔር ማንነት ሳንለያይ በደምና አጥንት የተሳሰረውን አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

”በየመድረኩ ሰላምና የህግ የበላይነት ስለተባለና ፍላጎት ስላለ ብቻ ያለ ተጨባጭ የጋራ ጥረት የሚመጣ ሰላም አለመኖሩን በመግለጽ፣ ያንን ማምጣት የመንግስት ስራ ብቻ አድርጎ ከማሰብ ሁሉም በጋራ ሊሰራ እንደሚገባ አክለዋል።

በተለይም የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የጋሞ አባቶችና እናቶች ተንበርክከው ሰላምን እንዳስጠበቁ “ሌሎቻችሁም ተንበርከኩና ትውልድን ታደጉ” ሲሉም በአጽንኦት ጠይቀዋል አፈ ጉባዔዋ።

“ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በዓለም ዙሪያ ሰላም በማስከበር የምትታወቅ አገር ናት” ያሉት አፈ ጉባዔዋ ለትውልድም ሊተላለፍ የሚገባው ይህ መልካም ስራና ስም ነው ብለዋል።

ከፊታችን እየመጣ ያለውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንንም በእርቅና በሰላም ስነ ልቦና ቀይሮ አንድነታችንን ወደ ነበረበት በሚመልሰው መልኩ ማክበር ይገባናልም ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.