ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ዘርፍ ብቃታቸውን ማሳየት ቀጥለዋል

ኢትዮጵያዊያን በድል ያጠናቀቁበት የአፕሳ አፍሪካዊያን ወጣቶች የፈጠራ ውድድር

ካሳለፍነው አርብ አንስቶ ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲደረግ የቆየው የአፕሳ አፍሪካዊያን ወጣቶች የፈጠራ ውድድር “APSA Science and Technology Challenge Ethiopia 2018” ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን አሸናፊ በማድረግ ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሣይንስ አካዳሚ ባዘጋጀው በዚህ ዝግጅት ላይ ከመላው አፍሪካ ለመጨረሻው ዙር ተጣርተው የቀረቡ 11 የካሜሮን፣ ቤኒን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ቶጎ፣ እና ዩጋንዳ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነውበት ነበር፡፡ በውድድሩ መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረ ማርያም ከእሳት እና ቁሳቁሶች መፈጠር አንስቶ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በሰው ልጆች ስልጣኔ ውስጥ ትልቅ ድርሻን እንደተጫወተና ከታዳጊ ሃገራት የዕድገት ጉዞም አይተኬ ሚናን እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡ በማስከተልም ወጣቶቹ በያዙት በጎ ተግባር እንዲቀጥሉበት አሳስበው መልካም ምኞትን ተመኝተውላቸዋል፡፡
በውድድሩ ላይ የአንደኝነት ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የ2010 የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በሆነችው ሃና ጥላሁንና አራት ሴት ጓደኞቿ አማካኝነት ተሰርቶ የቀረበው የእናቶችን ምጥ መቆጣጠሪያ ወይም “Augmentation and Induction Monitoring Device” ነው፡፡ የእናቶችን የምጥ መጠን በመለካት ምጥ የሚቆጣጠረው ይህ መሳሪያ ጥቅሙ ለዕናቶችና ህፃናት ብሎም ለአዋላጅ ነርሶች እንደሆነ የፈጣሪዎቹ እምነት ነው፡፡ ከእነርሱ በመቀጠል ሁለተኛ የወጣው የኢትዮጵያን ባህላዊ የሽመና ማሽንን በማዘመን ላይ ያተኮረ ስራ ሲሆን ዕርቅ እስከመቼ እና ጓደኛው በጋራ ያከናወኑት ነው፡፡ በሶስተኝነት ያጠናቀቀው የካሳቫ ተክልን ቆሻሻ አልባና ከሰው ንክኪ በፀዳ መልኩ የተለያዩ ምርቶችን እንዲሰጥ የሚያስችል የአንድ ካሜሮናዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ፈጠራ ውጤት ሆኗል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.