ከአሁን በውኀላ አህዳዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አይመለስም

የኦሮሞ ህዝብ ሀገራችን ለደረሰችበት የለዉጥ እና የተስፋ ምዕራፍ ከወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን መራራ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍሏል፡፡

የህዝባችን ዋና ዋና የትግል አጀንዳዎች ነጻነት እንዲሰፍን፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የግል እና የቡድን መብቶች እዲከበሩ፣ ዜጎች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ የተደራጀ ሌብነት እንዲቆም፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሰፍን…ወዘተ የሚሉ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድም ቀን ፌዴራሊዚም ስርዓቱን ተቃርኖ ቆሞ አያውቅም፡፡ ፓርቲያችን ኦዲፒም ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሁለት ጽንፎች የሚቀነቀኑ የመገንጠልም ሆነ አሀዳዊ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የኦሮሞን ህዝብ ህዝብ የማይጠቅሙ ከመሆናቸውም በላይ የሀገራችንን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና ወደፊት የማያራምዱ ናቸዉ ብሎ ያምናል፡፡ ሰለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በከፈው መስዋእትነት እየተገነባ ያለዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲጎለብት ጠንክሮ ይሰራል፡፡

የህዝባችንን የትግል አጀንዳዎች ከግብ በማድረስ ሁሉም በእኩልነት፣ በነጻነት እና በወንድማማችነት የሚኖርባት ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ኦዲፒ ከሌሎች ዴሞክራቲክ ሃይሎች ጋር በመትጋት ላይ ይገኛል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብትና ጥቅሞች ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማጠናከር፣ እውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በሰለጠነ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይከበራል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በጽናት በመታገላችንን እንቀጥላለን!

አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.