ዘለፋ ዛቻ ጥላቻ የትም አያደርሰንም

አቧራው ሲረግብ መንገዱ ይጠራል!

በማንም ሰው ላይ ጥላቻ የለኝም። በቀላሉ የምገፋም ሰው አይደለሁም። አሸዋ ላይ አልቆምኩም! ዘለፋ፣ ፍረጃ፣ ጥላቻ፣ ዛቻ… ትክክል ነው ብዬ ባላምንም ተጠራጣሪነት የፈጠረው ስጋት በተለያየ መልኩ እየተገለጠ እንደሆነ ነው የምረዳው። ዛሬ ለውጡን የሚመራው አካል ከኦሮሞ የወጣ ቡድን ባይሆን ራሱ እንዲሁ በጥርጣሬ እየታያየን ብዙ መባባላችን አይቀርም ነበር። እያንዳንዷን ድርጊት እንደፀጉር እየሰነጠቅን መወጋገዛችን ከአሁኑ አይለይም ነበር። የትናንቱ ጦስ ስነልቦናችን ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል። ያለፈው ጠባሳ ያልሻረለት በርካታ ኢትዮጵያዊ ዛሬም ትከሻውንን እያየ ተሳቆ ቢሄድ፤ ሁሉ ሁሉን ቢጠራጠር ገራሚ አይሆንም!

ይህ እንደማህበረሰብ ያጋጠመን ችግር ነው። ያለፉት ገዢዎቻችን በተለያየ መልክ ገዝግዘው ያጠፉት አንዱ እሴት መተማመንን ነው። ሁላችንም የዚህ ሰለባ ሆነናል። እኔ የምደክመው ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ይህ የለውጥ ዕድል ዳግም ከጃችን እንዳይወጣ ነው። ፍፁም ነኝ ብዬ አላምንም – ብዙ ልሳሳት እችላለሁ – ሰው ነኝ። ሁሉንም በእኩል ለምታቅፍ ኢትዮጵያ ይበጃል የምለውን ከማድረግ ግን ቅንጣት አልሰስትም። አዲሲቷን ኢትዮጵያ እናፍቃለሁና። በሰው ልጅም ተስፋ አልቆርጥም – የማይለወጥ የለምና። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደመሃል ይመጣል። ሊበራሊዝም ይለመልማል!

ይህን አቋም የሚጋሩኝን በስልጣን ላይ ያሉም የሌሉም ሀይሎች እንዲሳካላቸው መመኘት ብቻ ሳይሆን አቅሜ በፈቀደ ሁሉ እደግፋቸዋለሁ። ወጀቡ ሲያልፍ በጠራው ሰማይ በውቡ ባህር ልጆቻችን ይቦርቃሉ – አቦራው ሲረግብ በጠራው መንገድ በህብረት ለሰው ልጅ እድገት በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ! እንዲህ እንዲህ እያልን ዛሬ በፍቅር እና በተስፋ የምንፈጥረው ነገ ብሩህ ይሆናል! ወዳጄ ይኸው ነው!

ሁላችሁም ክቡር የሰው ልጅ ናችሁ – ፍቅር ለሰው ሁሉ!

✌ Yonathan tr

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.