ልጅ እያለሁ እጅግ አራስወዳድ ነበርኩ

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ
“የአባቴ ሦስቱ ምክሮች”

የወቅቱ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ ጥሩ ስትራቴጂ አዋቂና የሀገር መሪ ብቻ አይደሉም፡፡ ጥሩ ወግ አዋቂ ጭምር እንጂ፡፡ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ስለልጅነት ጊዜያቸው ተናገረዋል፡፡
“ልጅ እያለሁ፣ እጅግ በጣም ራስ ወዳድና ሁሉንም ነገር ለኔ ባይ ነበርኩኝ” ይላሉ ፕሬዝዳንተ ሺ ጨዋታቸውን ሲጀምሩ፡፡ ለግማሽ ክፍለዘመን ወደኋላ በትዝታ እያሰቡ ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡
ራስ ወዳድ ከመሆኔ የተነሳ ሁል ጊዜም ጥሩ ጥሩውን ለራሴ ነበር የምወስደው፡፡ ይህ ባህሪዬ ቀስ በቀስ ጓደኛ እያሳጣኝ መጣ፡፡ በመጨረሻም ጓደኞቼ ሁሉ ሸሽተውኝ ጓደኛ አልባ ሆንኩ፡፡ እኔ ግን ጥፋቴ ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ጓደኞቼ ስለሸሹኝ ኮነንኳቸው እንጂ ጥፋቴ ምን እንደሆነ ራሴን አልጠየኩም፡፡ ቢሆንም፣ አባቴ ሕይወትን በመልካም መንገድ እንዴት መምራት እንደምችል በተግባር አስተማረኝ፡፡
የአባቴ የሕይወት ትምህርት ሶስት ደረጃዎች ነበሩት፡፡
አንድ ቀን አባቴ፣ ለሁለታችን የሚሆን ምግብ አዘጋጀና በሁለት ሳህን ከፍሎ የምግብ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠው፡፡ ምግቡ ፓስታ (ኑድል) በእንቁላል ነበር፡፡ አባቴ ፓስታውን ሲያስቀምጠው በአንደኛው ሳህን ከፓስታው በተጨማሪ የተቀቀለ አንድ እንቁላል ከአናቱ አድርጎበታል፡፡ በሌላኛው ሳህን ግን ከፓስታው በላይ እንቁላል የለም፡፡ ከዚያ አባቴ ወደ እኔ እየተመለከተ፣ “ልጄ የትኛውን ትፈልጋለህ? አንዱን ሳህን ምረጥ” አለኝ፡፡
በጊዜው፣ እንቁላል እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ ምግብ አይደለም፡፡ አዲስ ዓመት ካልመጣ ወይም ዓመትባል ካልደረሰ በቀር እንቁላል መብላት ዘበት ነው፡፡ ፈጥኜ እንቁላል ያለበትን ሳህን መረጥኩ፡፡ በሰዓቱ፣ ሳህኑን ሳነሳ ቅንጣት ታህል አላመነታሁም፡፡ ደስ እያለኝ መብላት ጀመርኩ፡፡
አባቴ ሁለተኛውን ሳህን አንስቶ መመገብ ሲጀምር አይኔን አላመንኩም፡፡ አባቴ ከሚበላበት ሳህን ውስጥ ሁለት የተቀቀሉ እንቁላሎች በፓስታው ተሸፍነው ኖሯል፡፡ ተቆጨሁ በጣም! ቸኩዬ በመወሰኔ ራሴን ወቀስኩት፡፡
ይሄን ጊዜ አባቴ እየሳቀ፣ “የኔ ልጅ፣ አይኖችህ የሚያዩት ሁሉ እውነት እንዳልሆነ መቼም እንዳትረሳ! በሰዎች ላይ ብልጣብልጥ ለመሆን ስትሞክር ትጎዳለህ!!” አለኝ፡፡
በሌላ ቀን፣ አባቴ በተመሳሳይ ምግብ አዘጋጅቶ ሲያበቃ እንደተለመደው ፓስታውን በሁለት ሳህን አቀረበው፡፡ አንደኛው ሳህን አናት ላይ አንድ የተቀቀለ እንቁላል አስቀምጦበታል፡፡ በሌላኛው ግን ከላይ ምንም እንቁላል አላደረገበትም፡፡ ከዚያ እንደተለመደው አባቴ ወደ ምግብ ጠረጴዛው እየጠቆመ “ልጄ፣ ምረጥና የምትፈልገውን ሳህን ውሰድ” አለኝ፡፡
ካለፈው ስህተቴ በመማር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብኝ አሰብኩና ቀልጠፍ ብዬ ከአናቱ እንቁላል የተደረገበትን ትቼ ሌላኛውን መረጥኩ፡፡ ከዚያ በፍጥነት ፓስታውን ገላለጥኩና ሳህኑን አየሁት፡፡ በጣም ደነገጥኩ! ሳህኑ ውስጥ አንድም እንቁላል የሚባል ነገር የለም፡፡
አባቴ በድጋሚ እየሳቀ፣ “ልጄ፣ ሁል ጊዜ በልምድህ ላይ ብቻ የምትተማመን ከሆነ ትከስራለህ፡፡ አንዳንዴ ሕይወት ራሷ ልታሞኝህ ወይም ቁማር ልትጫወትብህ ትችላለች፡፡ ዳሩ ግን፣ በዚህ ብዙ ልታዝን ወይም ልትቆጣ አይገባም፤ ትምህርት እንደሚሆንህ ቆጥረህ እለፈው፡፡ እንዲህ ያለውን እውቀት ከመማሪያ መፅሀፍት ላታገኝ እንደምትችል አስታውስ” ብሎኝ፣ ያ ቀን አለፈ፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ አባቴ ምግብ አዘጋጀ፡፡ እንደተለመደው ፓስታ እና እንቁላል በሁለት ሳህኖች ቀርበዋል፡፡ በአንዱ ሳህን የተቀቀለው እንቁላል ከፓስታው በላይ ተቀምጧል፡፡ በሌላኛው ሳህን ደግሞ ፓስታ ብቻ…፡፡ የውስጡን አላውቅም፣ ከላይ ግን እንቁላል የለም፡፡ አባቴ የተለመደው ጥያቄውን አቀረበልኝ፡፡ ወደ ምግብ ጠረጴዛው እየጠቆመ፣ “ልጄ ምረጥ! የትኛው ሳህን ይሁንልህ?” አለኝ።
አሁን እኔ ከሁለት ሥህተቶቼ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡
“አባቴ አንተ የቤቱ አባወራ ነህ! ለቤተሰባችን ሰርክ የምትለፋ አባት ነህ፡፡ መጀመሪያ መብላት ያለብህ አንተ ነህ፤ ይገባሃልም፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ አንተ አንሳ…” ስል መለስኩለት፡፡
አባቴ በጭራሽ አላቅማማም…፡፡ ከአናቱ እንቁላል የተቀመጠበትን ሳህን አንስቶ መብላት ጀመረ፡፡ እኔም ሁለተኛውን አንስቼ ፓስታዬን ለመብላት አቀረቀርኩ፡፡ እርግጠኛ ነበርኩ፣ ሳህኑ ውስጥ እንቁላል እንደማይኖር፡፡ ከፓስታው በታች ሁለት እንቁላሎችን ሳገኝ ግን አይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡
ቀና ብዬ ሳየው፣ አባቴ ፈገግ ብሎ በፍቅር አይኑ እያስተዋለኝ ነበር፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል መከረኝ፤ “የኔ ውድ ልጅ! ለሌሎች ሰዎች መልካም መልካሙን ስታደርግ ተፈጥሮ ራሷ መልካም መልካሙን ወደ አንተ ታመጣለች! ይሄንን መቼም እንዳትዘነጋ” አለኝ፡፡
ከዚያን ጊዜ በፊትም ሆነ፣ ከዚያን ጊዜ በኋላ አባቴ ብዙ ጊዜ መክሮኛል… ገስፆኛል፡፡ አብዛኞቹን ማስታወሴን እጠራጠራለሁ፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ ሦስት ምክሮቹን በፍፁም አልረሳቸውም… እስክሞት ድረስ፡፡ እነሆ ሕይወቴም በዚህ ምክንያት የተስተካከለ ሆኗል፡፡ ከአባቴ ምክር በኋላ ስኬት መንገዷን ወደ እኔ አድርጋለች፡፡
አባቱን የሚወድ ሼር
ምንጭ: Long Live Ethiopia

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.