አራቱ ሚስቶች

አራት ሚስቶች የነበሩት አንድ ሀብታም ነጋዴ ነበር፡፡ አራተኛ ሚስቱን ከሌሎች አብልጦ በእጅጉ ይወዳታል፡፡ ስለሚወዳትም ጥሩውን ሁሉ ለእርሷ በመስጠት ይንከባከባታል፤ያስደስታታል፡፡ ሦስተኛ ሚስቱን መውደድም ብቻ አደለም ይኮራባታል፣ ይመካባታልም ጭምር፡፡ ይዟት በአደባባይም ለመታየት ይፈልጋል ነገር ግን ጥላው እንዳትሄድ በጣሙን ይሰጋል፡፡ ሁለተኛ ሚስቱንም እንዲሁ ይወዳታል፡፡ ይች ሁለተኛ ሚስቱ በነገሮች አስተዋይና ብልህ ታጋሽም በመሆኗ ይመካባታል፡፡ ነጋዴው አንዳች እክል የገጠመው እንደሁ ችግሩን ታቅፎ እሚያመራው ወደ ሁለተኛ ሚስቱ ነው ፡፡ እሷም በአስቸጋሪው ሰዓት ከጭንቀቱ ትገላግለዋለች፡፡ የመጀመሪያ ሚስቱ በጣም ታማኝ አጋሩ ናት፡፡ ቤቱንና ንግዱን የምትመራለትና የምታስተዳድርለት እሷው ነች፡፡ እሷ በጣም የምታፍቅረው ቢሆንም እሱ ግን ስለማያፈቅራት አንድም ቀን በትውስታው ውስጥ ቦታ ሰጥቷት አያውቅም ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ህመም ተሰማውና ማለፉን ባሰበ ጊዜ የተድላ ዓለሙን እያስታወሰ እንዲህ አሰበ “አራት ሚስቶችና የተትረፈረፈ ሀብት አለኝ ነግር ግን በሞት ጊዜ ብቻየን እሆናለሁ፡፡ እንዴት ብቻየን እሆናለሁ?” በማለት አራቱንም ሚስቶች በማስጠራት ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡

“ሁላችሁንም በጣም እወዳችኋለሁ:: የሚያምሩ አልባሳትንም እያለበስኩ ሳስጌጣችሁ ኖርኩ፡፡ አሁን ግን ልሞትናውና ከብቸኝነቴ ታድኑኝ ዘንድ ተከተሉኝ” አላቸው፡፡ አራተኛው ሚስቱ “በፍጹም አይሆንም” ስትል መልሱን ሰጥታው ከአካባቢው ተሰወረች፡፡ ነጋዴው በሰማው ምላሽ ልቡ ተነካ፡፡ ለሦስተኛዋ ሚስቱ “በሕይዎቴ ሙሉ ስወድሽ ኑሪያለሁ አሁን አብረሽኝ ልትሆኝና ወደምሄድበት ልትከተይኝ ትፈቅጃለሽ?” አላት በአዘኔታ ሁኖ መልስ ሲጠባበቅ “አይሆንም ሕይዎት አትጠገብም ፡፡ እዚህ መኖር መልካም ነው፡፡ እናም ከአንተ ሞት በኋላ አግብቸ መኖር እሻለሁ” አለችው፡፡ ይህ ሀብታም ነጋዴ ልቡ ዝቅ ሲልና ወደ ቀዝቃዛነት ሲለወጥ ተሰማው፡፡ አሁንም በተስፋ መቁረጥ ሁኖ “በሕይዎቴ ሙሉ እርዳታን ስፈልግ ወደ አንች ስመላለስ ኑሪያለሁ፡፡ ስትረጅኝም ነበር፡፡ አሁንም እርዳታሽን ፈልጊያለሁና እርጅኝ” ሲል ሁለተኛ ሚስቱን ጠየቃት፡፡ “በዚህ ሰዓት ልረዳህ ባለመቻሌ አዝናለሁ፡፡ ማድረግ የምችለው አንተን ወደ መቃብርህ መሸኘት ብቻ ነው” ስትለው መብርቅ የመታው ያህል ክው አለ፡፡ በድንጋጤ ስሜት ተውጦ እያለ “የትም ብትሄድ እከተልሃለሁ፤ አንተጋ እሆናለሁ!” የሚል ድምጽ ሲያስተጋባ ተሰማው ዓይኑን ሲያነሳ የተጎሳቆለ እይታ ያላት የመጀመሪያ ሚስቱ ነበረች ነጋዴው ሳግ እየተናነቀው “ሲኖረኝና ስችል ልንከባከብሽ ይገባኝ ነበረ” በማለት እቅፍ አድርጎ ወደሰውነቱ አስጠጋት፡፡

በመሠረቱ ሁላችንም በሕይዎታችን አራት ሚስቶችን አኑረን ይሆናልና የእኛም ታሪክ ሊሆን ይችላል፡፡

1. አራተኛው ሚስታችን ፈራሹ ስጋችን ነው፡፡ ለምቾቱና ለውበቱ ተጨንቀን ብንደክምም ቀሪ እንጅ ተከትሎን አይሄድም፡፡

2. ሦስተኛው ሚስታችን አለን የምንለው ነገር ንብረት፣ ሀብትና ክብራችን ነው፡፡ ይሄም እኛ ስንሞት ወደሌሎች የሚተላለፍ ነው፡፡

3. ሁለተኛው ሚስታችን ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናችን የቱንም ያህል ቀረቤታና ቁርኝት ቢኖረንም ማድረግ የሚችሉት እስከ መቃብር መሸኘት ብቻ ነው፡፡

4. የመጀመሪያዎ ሚስታችን ሕያው ነፍሳችን ናት፡፡ ቁስና ሀብት ስናሳድድ ወደ ጎን ገፍተናት ቢሆንም አብራን የምትሆነው እሷው ነችና በመጨረሻው ሰዓት ሳይሆን አሁኑኑ እንድናለመልማት ያስፈልጋል ነው ያታሪኩ ጭብጥ፡፡

ምንጭ፡ The Four wives

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.