መንታ መንገድ

መንታ መንገድ
ክፍል ስምንት

.
.
ባህርዳር ፓፒረስ ሆቴል ከራሄል ጋር አንድ ክፍል ዉስጥ ነን። ራሄል ሙሉ ራቁቷን ከፊት ለፊቴ አልጋዉ ጋር ቆማለች። በሩን ተደግፌ አየኋት። አንድ ከዉብም ዉብ የሆነች ለፍቅር የምትከጅለኝ ሴት መቋቋም የማልችለዉን ዉበቷን ከፊቴ ደቅናብኛለች። የሴት ልጅ ራቁት ገላን የሚደርስ ዉበት ምድር ላይ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ። እኔ እንኳን ዝሙት ልፈፅም ከቤተሰቤ ዉጪ የሆነች ሴት ልጅን እንኳ ጨብጬ አላዉቅም። ጨዋነቴን ደሞ ራሄል ራሷ ትመሰክራለች። ራሄል በእጆቿ እንድቀርባት ምልክት እያሳየች ተጠጋችኝ። ምን እያደረገች ነዉ? ልቤ ቀጥ አለ። ተጠጋችኝ! አተነፋፈሴ ዝብርቅርቁ ወጣ። በጣም ቀረበችኝ! ተሸነፍኩ። ያለምንም ጦር መሳሪያ በራቁት ገላዋ አስገዳጅነት ልብሴን ራሴዉ ማዉለቅ ጀመርኩ። “አክረም ሀይማኖትህስ?” ይላል ህሊናዬ! “ሀይማኖት ምን ነበር? ሀይማኖት? ሀይማኖት? አላወቅኩትም!” ብዬ እክዳለሁ። ህሊናዬ ጥያቄዉን አያቆምም “እሺ ሀይማኖተኛ አይደለህ ጌታህን አትፈራዉም?” ይለኛል። “ጌታ ማነዉ?” ብዬ የትም እንደማላዉቀዉ ለህሊናዬ እነግራለሁ። የሴት ዉብ ገላ ከፊትህ ቀርቦ ፈጣሪህን ልታስብ አትችልም። አሁን የፈጣሪ ትዕዛዝ በደንብ ገባኝ። ለምን ዝሙትን አትቅረቡ እንጂ አታድርጉ የሚለዉን ቃል እንዳልተጠቀመ ተረዳሁ። ዝሙት ደጃፍ ላይ ተቁሞ ዝሙትን አልሰራም ማለት ዘበት ነዉ። ራስን ነፃ ለማዉጣት ዉሳኔ የመወሰን አቅም የሚኖረን በሩ ላይ ሳንደርስ ከሩቁ ሲሆን ብቻ ነዉ። ነብዩ ዩሱፍ(ዮሴፍ) እራሱ የዝሙት ግብዣ እሱናጋባዧ ብቻ በነበሩበት ዝግ ቤት ዉስጥ የቀረበለት ጊዜ ልቡ ከጅሎ ነበር። ግን ነብይ ነበርና ፈጣሪ የነገሩን መጥፎነት አመላከተዉ።
ራሄል ቦዲዬን በማዉለቅ ተባበረችኝ። ሁለታችንም ራቁታችንን ቆምን። ራሄል እጄን እየጎተተች ወደ አልጋዉ ወሰደችኝ። አንገቴን ይዛ ወደ ከንሮቼ ከንፈሮቿን አስጠጋች። አንዴ ስትስመኝ ሰዉነቴን ለየት ያለ የቁጣ ስሜት ወረረዉ። በጥፊ ብዬ አልጋዉ ላይ ዘረርኳት። ሪቾ በጣም ደነገጠች። እኔ ግን አሁንም ፍላጎቴ እንዳለ ነዉ። ወደ አልጋዉ ስወጣ ሪቾ ተፈናጥራ ከአልጋዉ ወረደችና ልብሷን እንደነገሩ ለባበሰች። ምንድነዉ የተፈጠረዉ? ለምን በጥፊ መታኋት? ልቤ እኮ ሊያቅፋት ነበር የፈለገዉ። አካሌን ማን አዘዘዉ? ግራ ገባኝ። ሪቾ በግርምት ቆማ አየችኝና “በጣም ይቅርታ!” አለችኝ። ምን ብዬ የተፈጠረዉን ነገር እንደማስረዳት አላዉቅም። “ልመታሽ ፈልጌ አልነበረም!” አልኳት ቱታ ሱሪዬን እየለበስኩ። አንዳችን ጭንቅላታችንን በላይ በኩል ሌላችን በታች አድርገን በተለያየ አንሶላ ለመተኛት ተስማማን። ሪቾ በጥፊ የመታኋት ከሷ ጋር መተኛት ስላልፈለግኩ እንደሆነ አስባ ያቀረበችዉ አማራጭ ነዉ። እኔ እጄን ማን እንዳዘዘዉ አላዉቅም እንጂ እንቢ የምልበት ምንም አቅም አልነበረኝም።
.
ልክ በተቃራኒ አቅጣጫ እንደተኛን ሪቾ “አክረሜ ይሄ አንተን የኔ ለማድረግ የወሰድኩት እርምጃ ነበር። ባለጌ አይደለሁም ታዉቃለህ! ግን ፉክክሩ ከሀያት ጋር ሆነና በጣም ከበደ። ስለዚህ አንተን ለማሳመን ጊዜ ከመፍጀት ይልቅ እሷን በፈቃዷ እንድትተዉህ ማድረግ ነበረብኝ። ሀያት ዛሬ የተፈጠረዉን ነገር ስታዉቅ ራሷ ትተዉሀለች። ያኔ የኔ ብቻ ትሆናለህ።” አለችኝ።
ንግግሯ ዉስጥ የተጠና ስሌት ነበር። “እና ዉጪ አምሽተሽ አብረን እንድናድር ያደረግሽዉ አዉቀሽ ነዉ?” አልኳት ብሽቅ እያልኩ።
ተንጠራርታ ቦርሳዋን ከአልጋዉ ጎን ካለዉ ጠረዼዛ ላይ አነሳችና ከዉስጡ ብዙ መቶ መቶ ብሮችና ኤቲኤም ካርድ አዉጥታ እያሳየችኝ “አይደለም አንድ አንድ ክፍል ሁለት ሁለት ክፍል የሚያስይዝ ብር ይዤ ነበር። ግን እድሉን መጠቀም ነበረብኝ።” አለች። ወንድ ልጅ ከሴት ልጅ ጋር በተንኮል ሊፎካከር አይችልም። ሴትም ወንድን በጉልበት ልታሸንፍ አይቻላትም። አሁን ሪቾ ሁሌም ትለኝ የነበረዉ ነገር ትዝ አለኝ። “እኔ አንተን የራሴ ለማድረግ ምን ያህል መስዋዕትነት የምከፍል ይመስልሀል?” ነበር የምትለኝ። ዛሬ የት ድረስ እንደምትሄድ በተግባር አሳየችኝ። አሁን ሀያት ይህን ጉድ ካወቀች ምንም አልፈፀምንም ብላት እንዴት ነዉ የምታምነኝ? አንድ አልጋ ላይ ተኝተን ሳልነካት ወጣሁ ብላት እንዴት ነዉ የሚዋጥላት? እሷ ብትሆን ያደረገችዉ እኔም አይዋጥልኝም ነበር።
.
ሰማይ ሊጠራ ሰዓቱ 11:00 ሲል ከእንቅልፌ ባነንኩ። ሁሌም በዚህ ሰዓት የንጋት ስግደት ስለምሰግድ ከእንቅልፌ እነሳለሁ። ሪቾ ቀልቧን ስታ ተኝታለች። ፀጉሯ ብትንትን ብሎ ፊቷን በከፊል ሸፍኖታል። ግንባሯን ልስማት ፈለግኩና ትነቃለች ብዬ ፈርቼ ተዉኩት። አንዱን እግሯን እግሬ ላይ ሰቅላዋለች። ከንፈሮቿ ያሳሳሉ። ከዚህ በላይ ካየኋት እንዳልሳሳት ስለፈራሁ አይኔን ሰብሬ ሪቾን ላለመረበሽ እየተጠነቀቅኩ ከአልጋዉ ወርጄ ወደ መታጠቢያ ቤት ሄድኩ። መጀመሪያ ገላዬን ከታጠብኩ በኋላ ዉዱዕ አድርጌ ከመታጠቢያዉ ወጣሁ። “ዉዱዕ” ከስግደት በፊት የሚደረግ ትጥበት ነዉ። ጃኬቴን መሬት ላይ አንጥፌ ሰገድኩ። ከወንጀሎች ሁሉ ከባዱ ወንጀል ዝሙት አፋፍ ላይ የተሰገደን ስግደት ፈጣሪዬ ይቀበለኝ ይሆን? አላዉቅም። ሪቾ አሁንም እንደተኛች ናት። ቀን የበላችዉ ምግብ አልተስማማትም መሰል ደጋግማ ትፈሳለች። ገረመኝ! የእዉነት ቆንጆ ሴቶች የሚፈሱም ሆነ የሚፀዳዱ አይመስለኝም ነበር። መልዓክ ነዉ የሚመስሉኝ። ሽንት ቤት ደርሰን እንምጣ ሲሉ ራሱ መስታወት ላይ ፀጉራቸዉን ለማስተካከል እንደሆነ ነበር የማስበዉ። እንደዉም ሲመስለኝ ይሄ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ባለትዳሮች ችግር ነዉ። ቆንጆ ናት ብሎ ያገባና እንደሰዉ ስትሳሳት አሊያም ስትታመም ይደብረዋል። ምክንያቱም እሱ ያገባዉ አይኑ የገባች ቀን ያየዉን ዉበት እንጂ ትክክለኛ እሷነቷን አይደለም። ልትታመም ፣መልኳ ሊቀየር እንደሚችል አያስብም። ልክ እንደሱ ሰዉ መሆኗን ይዘነጋል።
.
አልጋዉ ጥግ ተቀምጬ ሲነጋ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስባለሁ። ሀያት ይሄን ታሪክ ካወቀች ለአይኗ ነዉ የማስጠላት! ራሄል ከእንቅልፏ እስክትነሳ ግጥም ለመፃፍ ስልኬን አበራሁ። የስልኬን ማስታወሻ ከፍቼ መፃፍ ጀመርኩ። ግጥሙን ጨርሼ የፊደል ስህተት ስለቅም ራሄል ከኋላዬ መጥታ ጀርባዬን አቀፈችኝ። ወይኔ አክረም! እጄን ለመጨበጥ ተሳስታ እጇን ከዘረጋች እንዴት ትሳቀቅ እንደነበር እኔ ነኝ የማዉቀዉ። ዛሬ ራቁቴን አቁማ ካየችኝ በኋላ ይኸዉ እንዳሻት በድፍረት ታቅፈኝ ጀመር። ስልኬን ቀምታ ግጥሙን ጮክ ብላ አነበበችዉ።
“አሸነፍሽኝ መሰል ፣ የልብሽ ደረሰ፣
እንቅልፍ ይዞሽ ጠፋ ፣ ፊትሽ ወዝ ለበሰ።
ሴት የማላዉቅ እኔን ፣ ልቤን ሲያርስ አደር ብለሽ ልታወሪ፣
ሀቅን በሴትነት ልታንበረክኪያት ፣ ነገር ልትዘዉሪ።
ነጋልሽ መሸብኝ እልል በይ፣ ተደሰች ግዴለም፣
ከፍ ያለ ይወርዳል የወረደ ይወጣል ፣ ሀሰት ፅኑ አይደለም።
ቆይ ግን ልጠይቅሽ
ከእሳት ስሜትሽ ላይ ፣ ዉሀን እንድቸልስ ምን ሀይል አስገደደኝ?
ገላሽን ላቅፍ ብዬ ፣ ጥፊ እንዴት ቀደመኝ?
ለዉብ ገላሽ ትዕይንት ፣ ለጣፋጭ ከንፈርሽ፣
ምን ይሉት ተዓምር ፣ ወንድነቴ እያለ ንዴቴን ላከልሽ?
ተይዉ አትንገሪኝ፣ መልሱን አዉቀዋለዉ።
ተበዳይ ቢተኛ ለሱ ሚቆምለት፣ ከላይ ጠባቂ አለዉ።”
“ተበዳይ ያልካት ሀያትን እንዳይሆን?” አለችኝ እየሳቀች። “ሰላማዊ ፉክክሩን እኮ ሁለታችንም ተስማምተንበት የጀመርነዉ መሰለኝ። ማሸነፍ መበደል አይሆንም!” አለችኝ። ራሄል ለማሸነፍ የመረጠችዉ መንገድ ምንም ከባድ ቢሆንም እሷ ግን በጣም ጨዋ መሆኗን እኔ እመሰክርላታለሁ። ራሄል ጨዋ ናት! አዎ ራቁ

ቷን ቆማ እንድተኛት ጠይቃኛለች ግን ጨዋ ናት! እዚህ ሁሉ ባለጌ ያስመሰላት ጣጣ ዉስጥ የከተትኳት እኔዉ ነኝ። አንዷን መርጬ አልያም ሁለቱንም አልፈልግም ብዬ ዉሳኔዬን መናገር እየቻልኩ በዝምታዬ የፉክክር ጣጣ ዉስጥ ጨመርኳት። ስለምትወደኝ የሷ ልታደርገኝ ያላትን ሁሉ ተጠቀመች።
“ቁርስ ልዘዝ ወይስ?” አለችኝ ሪቾ ተነስታ እራሷን እያስዋበች
“ኧረ ከሀዩ ጋር ነዉ የምንበላዉ እኔ ዶርም ማደሬን እኮ ነዉ የምታዉቀዉ!” አልኳት።
ተያይዘን ከፓፒረስ ወደ ፔዳ ግቢ ተሳፈርን። ሀሳቤ ቁርስ የምንበላበት ቤት ሆነን እነሀያት ጋር ለመደወል ነበር። ግቢ በር ጋር ከባጃጅ ስንወርድ ከነሀያት ጋር ተገጣጠምን። ሀዩ ፊቷ ቅይርይር አለ። ድንጋጤዬ ምላሴን አሰረዉ። ሀዩ እየሮጠች ሀጅራን እና እኛን በቆምንበት ትታ ወደ ግቢ ገባች። የራሄል እቅድ ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ሲሆን ተሰማኝ። ሀዩን ማጣት የለብኝም። እሷ የወደፊት ህይወቴም ሁሉ መሰረት ናት። በጠየቀችኝ ሰዓት ለማግባት አልፈለግኩም ነበር እንጂ ለትዳር ትክክለኛዋ ሴት ናት። ለምንድነዉ ሳጣት የምረዳት? ለምን?
.
ይቀጥላል…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.