መንታ መንገድ ክፍል 9

ክፍል ዘጠኝ
.
.
ሀያት ከራሄል ጋር ከባጃጅ ስወርድ ካየችበት ቅፅበት በኋላ ስልክ ስደዉልላት አታነሳም። በነጋታዉም ወደ ክፍል አልመጣችም። በጣም ጭንቅ አለኝ። ራሄል ልታገኘኝ ስልክ ብትደዉልም ማንሳት አልፈለግኩም። ክፍል ዉስጥ ስንገናኝ እናወራለን። ራሄል ምንም አላጠፋችም ግን ሀያትን እንደነጠቀችኝ ተሰማኝ። አሁን ከራሄል እና ከሀያት ትክክለኛዋ ምርጫዬ ሀዩ መሆኗን የተፈጠረዉ ክስተት በደንብ አረጋግጦልኛል። ዶርም ብቻዬን ተቀምጬ ከሀዩ ጋር ያሳለፍናቸዉን አስደሳች ጊዜዎች አስባለሁ። በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ባደረግናቸዉ ጉዞዎች ዉስጥ ያሳለፍናቸዉ ወርቃማ ጊዜያት አይኔ ላይ ድቅን ይላሉ። የሀያት ፍልቅልቅ ሳቅ አይኔን ይሞላዋል። በጨዋነቷ የታጀበዉ ፈገግታዋ ትዉስ ይለኛል። ምራቋን እየዋጠች “የሌላ ስትሆን ካየሁ ግን ሰዉ አልሆንም!” ያለችኝ ትዝ ይለኝና በራሴ እበሽቃለሁ። አዎን ሀዩ እንደድሮዉ ደስተኛናተጫዋች መሆን ከብዷታል። በርግጥ ከራሄል እና ከሀያት አንዷን ሳልመርጥ በዝምታ የቆየሁት ጓደኝነታችን ሊበጠበጥ ይችላል በሚል ስጋት ነበር። ዉጤቱ ግን ፉክክር ሆኖ አረፈዉ። ፉክክሩ ደሞ ጨዋዋ ራሄልን ራሱ ራቁቷን ፊቴ እስከመቆም አደረሳት። እዉነታዉን ልመልከት ብል ኖሮማ ሀያት ከራሄል ጋር የማትነፃፀርበት አንድ ትልቅ ከኔ ጋር የሚያመሳስላት ነገር አላት። ሀይማኖታችን አንድ አይነት ነዉ። እኔ ደሞ ሀይማኖቷ ከኔ የተለየችን ሴት አላገባም። አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ የሚለዉ አባባል የሚያምረዉ ዘፈን ላይ ብቻ ነዉ። መቻቻልን ለማሳየት የሀገር መሰረት የሆነዉ ቤተሰብ መናጋት የለበትም። ትዳር ልጅ የሚባል ፍሬ የሚያፈራ ተቋም ነዉ። ልጆችን ወደ አንዱ ሀይማኖት ለመዉሰድ በሚደረገዉ ሽኩቻ መሀል ልጆች ችግር ዉስጥ ሊገቡ አይገባም። ትዳሩም በሆይሆይታ ይጀመር ይሆናል እንጂ ባለመስማማት መጠናቀቁ አይቀርም። እስልምና ደግሞ የሌላ ሀይማኖት ተከታይ ማግባትን አይፈቅድም።
.
ሀዩን የተፈጠረዉ ነገር ላይ እጄ እንደሌለበት ለማስረዳት ቢያንስ እንዳገኛት ልትፈቅድልኝ ይገባ ነበር። እሷ ግን ስልኳን እንኳ አታነሳም። እንደ ድሮዉ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት አብሮ መብላት ቀረ። መንገድ ላይ ካየችኝ ራሱ መንገድ ትቀይራለች። ሀጅራ ሀያትን አንዴ እንኳን የምናገረዉን እንድትሰማኝ እንድታስማማት ብጠይቃትም ሊሳካላት አልቻለም።
.
ጁምዓ(አርብ) ትልቁ ኦዲተሪየም ዉስጥ የሚካሄደዉ የስነ ፅሁፍ ምሽት ላይ ስራዎቻችንን ለማቅረብ ከራሄል ጋር ሄድን። ዝግጅቱ ተጀምሮ ታዳሚዉ ቦታ ቦታዉን ከያዘ በኋላ ሀያት እና ሀጅራ ገብተዉ ከአቅራቢዎች መቀመጫ በስተግራ በኩል ራቅ ብለዉ ተቀመጡ። ከራሄል ጋር አብረን ያደርን ጊዜ የፃፍኩትን ግጥም ባቀርብ ለሀያት እዉነቱን ለማስረዳት እንደሚረዳኝ አሰብኩ። ገጣሚዎች እየተጠሩ ስራቸዉን ማቅረብ ጀመሩ። የሪቾ ተራ ደረሰና ወደ መድረኩ ወጣች።
“ስርየት” ብላ የግጥሙን ርዕስ አስተዋወቀችና ጉሮሮዋን ከጠረገች በኋላ ግጥሙን ማንበብ ጀመረች
“የታመመ ልቤን የሚያሽረዉ አጥቶ፣
ዘወትር ሲሰቃይ መድሀኒትን ሽቶ፣
በአንድ ለሊት ፍቅር፣ ቁስሉን አጠፋኸዉ፣
በእጅህ ልስላሴ ፣ገላዬን አከምከዉ፣
በከንፈርህ ጠዓም፣ ምሬትን ገደልከዉ፣
ገላዬ ላይ ነግሰህ ፣ ሰላሜን መለስከዉ።
ልቤ ሰላም ሲያገኝ ፣ ሀሴት ሊያገኝ ነብሴ፣
ጉድለቴን ሚደፍን ፣ የሰመመን ልብሴ
ተቸረኝ ከፍቅርህ ፣ ጠፋን ምድርን ለቀን፣
ስርየት ሆነ ያኔ ፣ ፍቅርህን ስትቸረኝ!
የኔ ነሽ ስትለኝ! ” አለችና ወደ ቀጣዩ ግጥም ለመሻገር ወረቀቱን ገለፀችዉ። ሀያት ከዚህ በላይ ለመቆየት አቅም አጣች። እንባዋን በሂጃቧ እየጠረገች አዳራሹን ለቃ ወጣች። ሀጅራም ተከተለቻት። ይሄ ግጥም ሆነ ተብሎ ለሀያት አክረምን አንሶላ ተጋፍፌዋለሁ ብላ ለማሳመን ያቀረበችዉ መሆኑ ገብቶኛል። ደግሞም ተሳክቶላታል። እኔም ግጥም የማቅረብ እቅዴን ሰርዤ አዳራሹን ለቅቄ ወጣሁ። ዉጪ ላይ ሀጅራ ሀያትን አቅፋ ስታባብላት አገኘኋቸዉ። ልጠጋቸዉ ስል ሀጅራ ራሷ እንድርቅ በእጇ ምልክት ሰጠችኝ። ከሀያት ጋር ለመነጋገር ጥሩ ሰዓት አይደለም ብላ ስላሰበች ይመስለኛል እንድርቅ ምልክት ያሳየችኝ። ቆይ እኔንስ ማን ይረዳኝ? ለምን አንዴ እንኳን እንዳወራት አትፈቅድልኝም? ለምን? ብስጭቴ ጣራ ነካ። ወደ ዶርም ሄጄ ማንም እንዳያናግረኝ ተናግሬ በብርድልብሴ ተጠቅልዬ ተኛሁ። እንቅልፍ ግን የለም!
.
ጠዋት ላይ ሀጅራ ደወለችልኝ። የዛሬን አያድርገዉና ሌላ ጊዜ በዚህ ሰዓት ሀዩ ደዉላ ቁርስ አረፈድክ እያለች ትበሳጭብኝ ነበር። ሀያት እና ራሄል ላይ ላዩን ሰላም ናቸዉ ግን ዉስጥ ዉስጡን እንደድሮዉ አይመስሉኝም። ስልኩን አንስቼዉ “ሀጁ በአላህ ሀያት ላናግረዉ አለች በይኝ!” አልኳት። ምኞቴ ነበር።
“ወይ ላናግረዉ¡ ባክህ ወደ ቤት ልትመለስ ሻንጣዋን እያዘገጃጀች ነዉ የሆነ ነገር አድርግ።” አለችኝ። ሀዩ ፀፀቴን ከአቅሜ በላይ ልትከምርብኝ ነዉ! የክፍላችንን ሰቃይ በኔ ምክንያት ወደ ቤቷ ስትመለስ ከማይ ብሞት እመርጣለሁ።
“አሁን ዶርም ናት?” አልኳት ሀጅራን
“የደወልኩልህ ቁርስ ልንበላ ከግቢ ልንወጣ ስለሆነ ነዉ። እንግዲህ የሆነ ነገር አድርግ። ያለበለዚያ ትኬት ቆርጣ ወይ ዛሬ አሊያም ነገ እሄዳለሁ ብላለች።” አለችኝ። ሀዩ የሌላ ስሆን ካየችኝ ሰዉ እንደማትሆን አስቀድማ ነግራኝ ነበር። ትምህርት እስከማቋረጥ የሚያደርስ ህመም እንደፈጠርኩባት ሳስብ በጣም በራሴ ተበሳጨሁ። ሀዩን ማስቀረት ካልቻልኩ እኔ ራሴ ሰዉ አልሆንም። ሀጅራ ሲወጡ ሚስኮል እንድታደርግልኝ ተነጋግረን ስልኩን ዘጋችዉ።
.
ይገርማል ሀዩን ከአጠገቤ ማጣት እንዲህ ያመኛል ብዬ አስቤ አላዉቅም። በአቅራቢያችን ያሉ መልካም ነገሮችን ጥቅም የምንረዳዉ ስናጣቸዉ ነዉ።
ራሄል ደዉላ አብረን ቁርስ እንድንበላ ጠየቀችኝ። ራሄል በፉክክሩ ምክንያት በጓደኝነታችን መሀል የተፈጠረዉ ክፍተት እሷንም በጣም አሳስቧታል። እኔ ግን የሀጅራን ስልክ እየጠበቅኩ ስለነበር መብላት እንደማልፈልግ ነገርኳት። ራሄል ብዙ ጊዜ አልበላም ካልኳት ዉጪ ወጥታ በስርዓቱ አትበላም።
ሀጅራ ሚስኮል ስታደርግልኝ ከዶርም ተነስቼ ከግቢ ዉጪ ወዳሉት ምግብ ቤቶች ሄድኩ። ሀያት እና ሀጅራ ሁሌም የምንበላበት ቤት ቁርስ አዘዉ ተቀምጠዋል። ያይኔአበባ ለማስተናገድ ትንደፋደፋለች። የምትሰራዉ ምግብ ይጣፍጣል። ከኔ ጋር ደሞ ስለምንግባባ አንዳንዴ ቆንጆ ምግብ ስትሰራ እንድቀምስላት በእቃ ትሰጠኛለች። ሀያት እና እኔ ሁሌም ሳንዱች በወተት ነበር ቁርስ የምንበላዉ። ከነሀያት ፊት ለፊት ተቀመጥኩና ያይኔአበባን እያየሁ “ሳንዱችናወተት” አልኩ! ሀያት ቀና ብላ ስታየኝ ፊቷ ተቀየረ። ጠልታኛለች። ግን እዉነቱን ለማስረዳት ከዚህ የተሻለ ጊዜ አላገኝምና ከነበርኩበት ጠረጴዛ ተነስቼ ሀያት አጠገብ ተቀመጥኩ።
ሀዩ ምራቋን ዋጥ አደረገችና “ምን ፈለግክ?” አለችኝ።
“ሀዩ በአላህ ይሁንብሽ አንዴ ብቻ አዳምጪኝ! አንዴ ብቻ! ላስረዳሽ!” አልኩ በአይኔ እየተለማመጥኳት።
ሀዩ የንዴት ፈገግታ ፈገግ አለችና እንባዋ እየቀደማት “እንዴት እንደሳምካት ነዉ የምታስረዳኝ? እንዴት እንደረከስክላት ነዉ ወይ የምታብራራልኝ? ከኔ ጋር ለትዳር ለመተጫጨት ዝሙት ላይ እንዳንወድቅ እናትሽ ይኑሩ ምናምን አልክ። ከኔ ጋር ስትሆን ሀይማኖተኛ ሀይማኖተኛ ይሰራራሀል። እኔ እኮ በክብር አግባኝ ነበር ያልኩህ! የማግባት አቅሙ ነበረህ። ግን አንተ የትም መልከስከስን ነዉ የመረጥከዉ። እና ምኑን ነዉ የምታስረዳኝ?” አለችና እንባዋን በሂጃቧ ጠ

ርጋ ቀጠለች
“አክ

ረም ከአንተ ጋር ብዙ ህልም ነበረኝ። ቀጣይ ህይወቴን ያለምኩት አንተን የህይወቴ አንድ አካል አድርጌ ነበር። ሁሌም ከእንቅልፌ ስነሳ ማየት የምፈልገዉ አንተን ነበር። ዛሬ ግን ለአይኔም አስጠልተኸኛል። ደግሞም በፍፁም የኔ መሆን አትችልም!” አለችኝ። የኔ መሆን አትችልም ያለችኝ የማልወዳት መስሏት ከሆነ ብዬ “ለምንድነዉ ያንቺ የማልሆነዉ?” አልኳት።
ሙሉ አካሏን ወደኔ እያዞረች “ዝሙተኛ ወንዶች የዝሙተኛ ሴቶች ናቸዉ። የምትለዉን የቁርዓን አንቀፅ እኮ አንተዉ ነበርክ የምትደጋግማት። አሁን ቆሽሸሀል ለንፅህናዬ አትገባም። የኔ ላድርግህ ብል ፀቤ ከፈጣሪ ጋር ነዉ የሚሆነዉ።” አለችኝ። ሀዩ ስታወራ የከዳኋት ባሏ እንጂ ገና ለፍቅር የጠየቀችኝ አትመስልም። አንባገነን ናት። ሪቾ ግን ለማሸነፍ ነዉ የምትሞክረዉ እንደ ሀዩ አታለቃቅስም።
ዝም ብዬ ሳዳምጣት የነበረዉ ሴቶች እንደዚህ በስሜት ሲያወሩ ከወንዱ የሚፈልጉት ትኩረቱን እንጂ መልሱን አይደለም ብዬ ስላሰብኩ ነዉ። ስትጨርስ ቀስ ብዬ ማስረዳት ጀመርኩ። “አዎን ቆሻሻ ወንዶች የቆሻሻ ሴቶች ናቸዉ። ግን እኔም ራሄልም ቆሻሻዎች አይደለንም።” አልኳት።
“እንዴት ባክህ?” አለችኝ እያፈጠጠችብኝ። አሁን ለማዳመጥ ዝግጁ መሆኗ ስለገባኝ እኔናራሄል ዝሙት አለመፈፀማችንን እና የዛን ቀን የተፈጠረዉን ነገር አንድም ሳላስቀር አስረዳኋት።
ሀያት እንባ በእንባ ሆነች። ከተቀመጠችበት ብድግ አለችና መሬቱ ላይ በግንባሯ ተደፍታ ጌታዋን አመሰገነች። ለኔ ንፅህና ጌታዋን የምታመሰግን ሴት! እንደሀያት ያሉ ሴቶች ከሚሊየን አንድ ናቸዉ።
.
ቁርሱ እንደቀረበ ሀዩ እንደለመደችዉ የኔን ቆርሳ በላችብኝ። ደስ አለኝ። ታርቃኛለች ማለት ነዉ። ወዲያዉ “አኩሻ ግን” አለች።
“ግን ምን?” አልኳት ፈገግ እያልኩ።
“አሁን ታረቅን ብቻ ነዉ ሚባለዉ ወይስ?” አለች አይኗን በሀፍረት እየሰበረች።
ምን ለማለት እንደፈለገች ስለገባኝ “ሴሚስተሩ ሲያልቅ ኒካህ እናደርጋለን። እኔም ከአሁኑ ቤት እናገራለሁ አንቺም ንገሪያቸዉ።” አልኳት። በደስታ ልታብድ ምንም አልቀራትም። ወዲያዉ ስልኳን አንስታ ራሄል ጋር ደወለችና ጠራቻት። ሪቾ ስትመጣ እኔም እዛዉ አለሁ። አየችንና “ኦ ገባኝ ሀዩ አሸነፈች ማለት ነዉ?” አለችኝ። “አዎ” አልኳት አይን አይኗን እያየሁ። ሪቾ በጣም ፍትሀዊ ናት! አታለቃቅስም። ግን በጣም ትወደኛለች። እኔም ሀይማኖታችን ቢመሳሰል የመጀመሪያም የመጨረሻም ምርጫዬ ሪቾ ነበረች።
ራሄል እንደምንም ፈገግ አለችና “እንደዚህ አራታችንም የምንሰበሰብበት ቀን ናፍቆኝ ነበር።” አለች። ከዛም ራሷ የዛን ቀን እንዴት ዉጪ አብሬያት እንዳድር እንዳደረገችኝ ፣ ሀዩን ለማሳመን የተጠቀመቻቸዉን መንገዶች ተረከችልን። ሪቾ ሽንፈቷን በፀጋ መቀበሏ በጣም አስደሰተኝ። ሪቾ እኮ ጨዋ ናት ብያችሁ ነበር። ከቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አራታችንም እንደድሮዉ አንድ ላይ ቁርስ በላን።
.
ይቀጥላል…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.