መንታ መንገድ ክፍል 10

መንታ መንገድ
ክፍል አስር

.
.
ከሀያት ጋር ከታረቅንና ለመጋባት ከወሰንን በኋላ
በአራታችን መካከል የነበረዉ የቀድሞዉ የጓደኝነት መንፈስ
ተመለሰ።
ከሀያት ጋር ኒካህ ለማሰር መወሰኔን ቀድሜ ደዉዬ
የነገርኩት ለሰዒድ ነበር። ለልብ ጓደኛዬ! የእዉነት እኔ
ሳይሆን እሱ የሚያገባ ያህል ነበር የተደሰተዉ። በነገራችን
ላይ እህቶቼ መርየምና ኢስራዕ ከኔ ጋር ያላቸዉ ቅርበት
ጨምሯል። ቢያንስ በሳምንት ሶስት ቀን ይደዉሉልኛል።
.
የሀያት እህት መግፊራ ደወለችልኝና “የክፍለ ዘመኑን
ምርጥ ዉሳኔ ነዉ የወሰንከዉ!” አለችኝ እየሳቀች። እሷም
እንደእህቷ ፍልቅልቅ ናት።
“የእህትሽን ባል እንዲህ ነዉ የምታናግሪዉ? አክብሪኝ
እንጂ!” አልኳት እየሳቅኩ። በዉሳኔያችን በጣም መደሰቷን
ነግራኝ አንዳንድ ነገሮችን አወራን።
እኔ የመጀመሪያ ስራ ብዬ ያቀድኩት እህቶቼን ከሀዩ ጋር
ማስተዋወቅ ነዉ። እነሱ ከወደዷት እናቴ ላይ በጣም
ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ለነገሩ ከእናቴ ጋር ቀረቤታም
ስለሌለኝ እነሱዉ ቢጨርሱልኝ ይሻላል። ለእህቶቼ
ዉሳኔዬን ነግሬ የሀያትን ፎቶ ቫይበር ላይ ላኩላቸዉ።
በፎቶ ወደዋት ሊሞቱ ምንም አልቀራቸዉም። ስልኳን
ሰጥቼያቸዉ ተዋወቋት። በዉሳኔያችን መደሰታቸዉንም
ነገሯት። ይህቺ የደስታናየሀዘን መግለጫ በመንግስታት
ብቻ ሳይሆን በግለሰብም ደረጃም አለች።
.
ከእህቶቼ ጋር በደንብ ካስተዋወቅኳት በኋላ ለአባቴ ደዉዬ
ነገርኩት። አባዬ “ኒካህ ማሰርህ ደስ ይለኛል ግን የልጅቷን
መልክ ብቻ አይተህ ከሆነ አይሆንም።” አለኝ። በሱ
የደረሰዉ በኔ እንዳይደገም ብሎ ይመስለኛል። እናቴ ቆንጆ
ናት ግን ምንም ስርዓት የላትም። ይኸዉ ህይወቱን ሙሉ
ስታቆስለዉ እና ሲደበድባት አለች። ከዚህ ቀደምም
ወደፊት ሳገባ ስነ ምግባሯ ያማረ ሴት እንድመርጥ
መክሮኝ ያዉቃል። እኔም ከሀዩ ጋር ያለንን ቅርበት ፣ ስነ
ስርዓቷን ፣ ሀይማኖቷ ላይ ያላትን እዉቀት ስነግረዉ
“እንደዛ ከሆነች መህር(ጥሎሽ) አንድ ሚሊየን ብር
ብትጠይቅህ ደስ እያለኝ እኔ እሰጥሀለሁ።” አለኝ። አባቴ
ስልኳን ወስዶ ሀያትን አወራት። የሀያት ቤተሰቦችም
ደዉለዉ ብዙ ነገር አወሩኝ። እንግዲህ መተጫጨቱ
ተጧጡፏል።
እናቴ ቅር እንዳይላት ብዬ ደወልኩና ኒካህ ለማሰር
ማሰቤን ነገርኳት። “ልጅቷ ከየት ናት?” አለችኝ አስቀድማ!
ሰዉ አሁን ብሔር ላይ ምን እንዲህ ያጣድፈዋል? ድሮም
እኮ እናቴ ሸሯ ይቀድማል። ግን ደስ የሚለዉ የሀዩ
ቤተሰቦችና የእናቴ ብሔር ተመሳሳይ ነበር። እንጂማ
አይሆንም ብላ ቀዉጢ ትፈጥር ነበር። አዲስ አበባ ታድጎ
እንዴት ብሔር እንደ ዋና መስፈርት ይታያል? ድድብና ነዉ!
.
የሀዩ እና የእኔ ቤተሰቦች እነ ሀያት ቤት ተገናኝተዉ ጉዳዩ
ላይ መከሩበት። ኒካህ ልክ ሴሚስተሩ አልቆ በመጣን
በሳምንቱ እንዲደረግ እና ትምህርታችንን እስከምንጨርስ
በየቤታችን እንድንኖር ወሰኑ። ይህ ሁሉ ነገር ሲካሄድ እኔና
ሀዩ ባህርዳር ነን።
.
ዉሳኔያቸዉን ስንሰማ ትዳር ምን ያህል ቤተሰብ የበላይ
ጠባቂዉ ሆኖ ሲደግፈዉ ደስ እንደሚል ተረዳን። ምናለ
ሁሉም በስሜት ተቃጥሎ ፍቅረኛ የሚሉት የዝሙት
መንደርደሪያ ላይ ከሚቆምና ቁልቁል ተንደርድሮ ዝሙት
ዉስጥ ከሚዘፈቅ ቤተሰብ አጋብቶ ራሳቸዉን ሲችሉ
አብረዉ መኖር እንዲጀምሩ ቢያደርግ? ማህበራዊ
ቀዉሱን በጣም መቀነስ ይቻል ነበር።
አሁን እኔናሀዩ ፈተና ጨርሰን ወደ ሸገር ስንመለስ ኒካህ
እናስራለን። ይሄ ማለት ሀዩ ሚስቴ ሆነች ማለት ነዉ።
ኒካህ ከታሰረ በኋላ ብስማት አሊያም ብተኛት ዝሙተኛ
አይደለሁም። ሚስቴ ነቻ! ግን በቤተሰቦቻችን ዉሳኔ
መሰረት ትምህርት እስከምንጨርስ የምንኖረዉ በየቤታችን
ነዉ።
.
ራሄል የሀያት እና የኔ ጉዳይ መስመር ሲይዝ ፤ ዘወትር
ካልተነጠፍንልሽ ከሚሏት ወንዶች አንድ ጨዋ የሆነ
እስክንድር የሚባል የነሱ ቸርች ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት
ጀመረች። ከጎኗ የሲጃራ ፓኮ አዉጥቶ አንዱን የመምዘዝ
ያህል ነበር ያቀለለችዉ። ድሮም እኔን ብላ እንጂ እንኳን
የሱ ልትባል ቀርቶ አብሯት ስለቆመ የአደም ዘር በሙሉ
የሚኮራባት አይነት ዉብ ልጅ ነች። በርግጥ ትንሽ
ዉጥረቷን ለማርገብ እንዲረዳት ብላ እንጂ ልጁን
አፍቅራዉ አይደለም። እስክንድር የጓደኝነት ክበባችን
ዉስጥ ሲጨመር አምስት ሆንን። እስክንድር ተጫዋች
ነዉ። እኔ በጣም ተመችቶኛል። ኢኮኖሚክስ የሚያጠና
የሸገር ልጅ ነዉ።
.
ፈተና እንዳለቀ ወደ አዲስ ለመመለስ ተነሳን።
እንደተለመደዉ ሀጅራ ወደ ኮምቦልቻ በጠዋት ሄደች። እኔ
፣ ሀዩ ፣ ሪቾ እና እስክንድር ደግሞ አራት ሰዓት አካባቢ
ወደ አዲስ አበባ በረርን።
በረራዉ እንደተጀመረ ሀዩ ወደኔ ዞር አለችና “ለኒካሁ አንድ
ሳምንት አብሮ መኖር ለመጀመር አንድ አመት ከአንድ
ሴሚስተር ቀረን!” አለችኝ።
ገና ከአሁኑ ቀን መቁጠር መጀመሯ አሳቀኝ። ነገ አይንህ
ይበራል ቢባል ዛሬን እንዴት አድሬ እንዳለዉ አይነስዉር
ሆነችብኝ።
.
አዲስ አበባ በገባን በሳምንቱ እሁድ ቀን የኒካህ ዝግጅቱ
እንዲደረግ ተወሰነ። እኛ ቤት የድግሱ ዝግጅት ሰርግ ነዉ
የሚመስለዉ። ሞቅ አድርገዉታል። ገና ቅዳሜዉን ድንኳን
ደኩነዋል። ሴቶቹ ቤት ዉስጥ ግጥም እየገጠሙ ፣ ከበሮ
እየመቱ ጭፈራዉን ያስነኩታል። ሴቶቹ የሚገጥሙት
ግጥም ብዙዉን እኔን የሚያሞግስ ነበር። ከሰዒድ ጋር
ከሚጨፍሩበት ክፍል አጠገብ ትንሽ ቆመን ሰማናቸዉ።
መርየም ታወጣለች ሌሎቹ ይቀበላሉ።
“የወንድ ልጅ ሱሪ ፣ያልቃል ከጉልበቱ፣
አክረሜን አትንኩት፣ አንድነዉ ለእናቱ።
እንጀራዉን ጋግሩ ፣ በስሱ በስሱ
አክሩ እና ሀዩዬ ፣ እንዲጎራረሱ።” ይላሉ በየመሀሉ
ከበሮዉ ይደለቃል። ዜማቸዉ ቀልብን ይገዛል። የሚሏቸዉ
ግጥሞች እኔን ከማሞገስ ባለፈም ላላገቡት መልዕክት
የሚያስተላልፉ ነበሩ። ኢስራዕ እያወጣች ሌሎቹ
እየተቀበሉ
“በፌስቡክ በዋትስአፕ ፣ ከምትጀነጅናት፣
ምትወዳት ከሆነ ፣ ኒካህ እሰርላት።” ፈገግ አልኩና “ሰዒዶ
እኔ እንግዲህ ላገባ ነዉ ይሄ ላንተ ይመስላል።
ምትጀነጅናት ካለች መክረዉሀል።” አልኩት።
.
እኔ ከሰዒድ ጋር ለኒካሁ ቀን የሚያስፈልጉኝን አልባሳት
ገዛዝቼ ጨርሻለሁ። በተለምዶዉ ሙሽራዉ የኒካህ ቀን
ሙሽራዋን ወደቤቱ የማይወስዳት ከሆነና ከዛ በኋላ
በሰርግ ሊወስዳት ካሰበ ሙሽራዋ በኒካሁ ቀን ወደ ወንዱ
ቤት አትሄድም። እኛ ጋር ግን አባዬ ድግስ ስለደገሰና
እንዲደምቅ ስለፈለገ ሀያት መጥታ ትንሽ ድግሱን አድምቃ
እንድትመለስ አባቴ ከቤተሰቦቿ ጋር ተስማምቷል።
.
ኒካሁ ነገ ሊሆን ቅዳሜ ማታ ሁለት አሮጊቶች ድንኳኑ
ዉስጥ ቁጭ ብለዉ ያወራሉ። እኔ በድንኳኑ ጀርባ በኩል
ነኝ። አያዩኝም።
“ቆይ ልጁ መች ከሀያ አመት ዘለለ እና ነዉ ለጋብቻ
ያስሮጠዉ?” አለች አንዷ ሴትዮ
“ምን የዛሬ ልጆች ገና ቂጣቸዉን ሳይጠርጉ ነዉ ሚስት
ማለት የሚጀምሩት!” አለች ሁለተኛዋ አሮጊት!
ሳላስባንን በድንኳኑ በር በኩል እያለፍኩ አሮጊቶቹ እነማን
እንደሆኑ ተመለከትኩ። የአንዷ ልጅ ሳታገባ ዲቃላ
አንጠልጥላ ይዛባት መጥታ አሮጊቷ እያሳደጉ እንደሆነ
መርየም ነግራኝ ነበር። ታዲያ ምን ታድርግ ትዳርን
እንዲህ ቅዠት አድርጋ የምታሳይ እናት ካለቻት ሌላ
አማራጭ መፈለጓ አይቀሬ ነዉ።
ሁለተኛዋ ደግሞ ልጇ ብዙም ወጣ ያለ ባይሆንም ፍቅረኛ
እየቀያየረ ስሜቱን ሲያስታግስ የኖረ ነዉ።
አሁን የልጆቹ ዝቅጠት መነሻ ወላጆቹ መሆናቸዉ ገባኝ።
ገና ስለ ትዳር ሲነሳ የሆነ ሆረር ፊልም አድርገዉ
ያሳዩሀል። አንተ መወጣት የማትችለዉ የሀላፊነት መዓት
የተደረደረበት መጋዘን አድርገዉ ይነግሩሀል። ምንም ደስታ
የሌለበት የችግር መሰረት አድርገዉ ይስሉልሀል። ግን
እዉነታዉ ይሀ አይደለም። ትዳር ተፈጥ

ሯዊ ተቋም ነዉ።
የሰዉ ልጅ ስሜት በተፈጥሯዊ መንገድ መርካት አለበት።
ለዚህ ደግሞ ትዳር የመጀመሪያዉ እና የመጨረሻዉ
አማራጭ ነዉ። ይሄ ተቋም በቀላሉ እንዲመሰረት ወላጆች
ልጆቻቸዉን ሊያግዙ ይገባል። አሁን ግን ትዉልዱ የትዳርን
በር ጠርቅሞ የዝሙትን በር ከበረገደዉ ቆይቷል።
የተዘጋዉ በር ሊከፈት ግድ ይላል!!
.
በነጋታዉ አምስት ሰዓት አካባቢ ወደነሀያት ቤት ሄድን።
ኒካህ ስለሆነ ግርግር አላበዛንም። በሶስት መኪና ነበር
የሄድነዉ። ሰዒድም ከኛ ጋር መጥቷል። እነሀያት ቤት
ስንደርስ የሴቶቹ ጭፈራ ለጉድ ነዉ። መድረሳችንን
ሲያዉቁ ደግሞ ጭፈራዉን የበለጠ አደመቁት። ቤተሰቦቿ
በር ላይ ወጥተዉ ተቀበሉንና ወደ ዉስጥ ገባን። የሴቶቹ
የጭፈራ ድምፅ ይሰማኛል። እዚህ ደግሞ ሀዩን እያሞገሱ
እኔን ይነቁራሉ። ስገምት መግፊራ ትመስለኛለች አሊያም
ሌላ ሰዉ የሚያወጣዉ እንዲህ አሉ
“ለምነህ ለምነህ ፣ተሀጁድ ሰግደህ
እንዲሁም አልቀረህ ሀዩን አገኘህ።” ተሀጁድ በለሊት ሰዉ
በተኛበት የሚሰገድ ስግደት ነዉ።
ነቆራቸዉን ቀጠሉ
“ነጭ ትለብሳለች ፣ ነጭ ትወዳለች
እዉነት ለመናገር ትቦንሰዋለች።
እንቁላል ቢሰበር እንቁላል ይተካል፣
የኔማ ሀዩዬ ፣ አይኗ ብቻ ይበቃል።”
“ሰዒድ እየሳቀ ኧረ በግጥም ወረዱብን እኮ!” አለኝ።
“ሀዩን ሊሰጡንማ ቢገርፉንም እንችለዋለን።” አልኩት
እየሳቅኩ።
.
ገብተን ትንሽ እንደተቀመጥን የኒካህ ዝግጅቱ ተጀመረ።
በሀይማኖታዊ ስርዓቱ መሰረት የጋብቻ ንግግር በሀይማኖት
አዋቂ ተደርጎ ሀያት ጥሎሽ የምትጠየቅበት ሰዓት ደረሰ።
ለወጉ ሁለት ሺህ ብር አለች። ወዲያዉ ጥሎሹን ሰጥተን
የጋብቻ ወረቀቱ ላይ ተፈራረምን። ሀዩን አገባኋት። ልክ
ሀያት ያለችበት ክፍል ወረቀቱ ተልኮ ስትፈርም ሴቶቹም
ግጥማቸዉን ሁለታችንንም የሚያወድስ አደረጉት
” ከዚህ እስከመስጂዱ ወርቅ ይነጠፍበት፣
አክረምና ሀዩ፣ ይመላለሱበት።
ጥቁር ይወዳሉ ጥቁር ይለብሳሉ፣
ለሀቁ ከሆነ ይመጣጠናሉ።” በድቤ ታጅቦ በሴቶቹ ዉብ
ድምፅ ይቀለፃል። ከሁሉም ያሳቀኝ ግጥም
“ግቢያችሁን እጠሩት ዳር ዳሩን አጥር፣
እስከአሁን ፆመሀል ከእንግዲህ አፍጥር።” የሚለዉ ነዉ።
እስከአሁን ፆመሀል ያሉት ከሚስት ጋር ሊደረጉ ከሚችሉ
ነገሮች ሁሉ ነዉ። እና ይኸዉ በሀዩ አፍጥር(ፆምህን
ግደፍ) ማለታቸዉ ነዉ።
.
ቤተሰቦቿ ሀዩን ለኔ መፍቀዳቸዉን ለማብሰር ግንባሯን
እንድስማት እሷ ወዳለችበት ክፍል ይዘዉኝ ሄዱ። ሀዩ
በጣም ተዉባ በሚያማምሩ ሴቶች ተከባ ተቀምጣለች።
ራሄልም አብራት ነበረች። ሚዜ አይደለችም ግን ሀዩን
አጅባ ተቀምጣለች። ዛሬ ሪቾዬን ባገባ በጣም ደስ ይለኝ
ነበር። ሳያት አሳዘነችኝ። እኔን የምታጣበት ድግስ ላይ
መገኘቷ ግርም ብሎኛል። ምን አይነት መቻል ይሁን ፈጣሪ
የሰጣት? እስክንድር ጉዳይዋ እንዳልሆነ በደንብ
አዉቃለሁ። አይኗን ከኔ ለማዞር እንዲያግዛት ነዉ
የተወዳጀችዉ። ሪቾን ሳላስባንን አየኋትና የሀዩን
የአይንእርግብ ገልጬ ግንባሯን ሳምኳት። ሴቶቹ
እልልታዉን አቀለጡት። የማህበረሰቡን እሴት ስትጠብቅ
ወላጅ እንዲህ እልል እያስባለ ልጁን ያስምሀል።
.
ይቀጥላል…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.