መንታ መንገድ ክፍል 11

መንታ መንገድ
ክፍል አስራአንድ

.
.
ከሀያት ጋር የተጋባንበት እና ባለሚስት የሆንኩበት ቀን
አለፈ። የሴሚስተሩም እረፍት
አልቆ ወደ ባህርዳር ተመለስን። በኔና በሀዩ መካከል ብዙ
ነገሮች ተቀየሩ። ከድሮዉ
በተለየ ብቻችንን እናሳልፋለን። እንደልቤ አቅፋታለሁ።
እስማታለሁ። ታዲያ ሰዉ
በሌለበት ነዉ። ማንም እና ምንም ሀዩን መንካት
አይከለክለኝም። ምክንያቱም ሚስቴ
ነች!!
.
ቅዳሜ ከሰዓት ብዙ ጊዜ ጣና ነዉ የምናሳልፈዉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሯን
የሳምኳትም ጣና ዳር ተቀምጠን ነዉ። ከንፈር የሆነ ለየት
ያለ ጣዕም አለዉ። ለኔ የሀዩ
ከንፈር የምድር ምርጡ ጣዕም ባለቤት ነዉ። ምክንያቱም
ከሀዩ ዉጪ ሌላ ሴት
እንዲህ በወጉ ስሞኝ አያዉቅም። ያለዉድድር ከንፈሯ
አሸንፏል። በርግጥ ሪቾ አንዴ
ከንፈሬን ስማኝ ነበር ግን ላስታዉሰዉ አልፈልግም።
ካስታወስኩት ብዙ ነገሮች አብረዉ
ይታወሱኛል።
.
የሴሚስተሩ ማለቂያ ሲደርስ አባቴ ደዉሎ መርየም
ልታገባ መሆኑን አበሰረኝ። ታናሽ
እህቴ ፈለጌን ስለተከተለች ደስ አለኝ። የምታገባዉም ልጅ
በስነ ምግባሩ መልካም
የሚባል አይነት ነዉ። ኒካሁ በሌለሁበት ተደርጎ ሰርጉን
ክረምት ስመለስ ለማድረግ ነዉ
ያቀዱት። ህይወቴ በደስታ ተሞላች።
.
የሪቾ ፍቅረኛ እስክንድር ወደ ማታ ደዉሎ ላግኝህ አለኝ።
ምሽቱን ሀያት ቤተ መፅሀፍ
ስለነበረች ብቻዬን አገኘሁት። ግቢያችን ዉስጥ
ሜንላዉንጅ የሚባለዉ ቦታ ተቀምጠን
አንዳንድ ነገሮችን ካወራን በኋላ ሊያገኘኝ ወደ ፈለገበት
ጉዳይ ገባን።
“ራሄልን ግን በደንብ አስተዉለሀታል?” አለኝ ትኩር ብሎ
እያየኝ። እዉነት ለመናገር
ከጋብቻዉ በኋላ ብዙም ትኩረቴ ወደሷ አልነበረም።
በርግጥ የምግብ ሰዓቶች ላይ
እንደድሮዉ አብረን ነዉ የምንበላዉ።
ዝም ስለዉ “አኩሻ ጤናዋ እየተዛባ ነዉ።” አለኝ።
“እንዴት?” አልኩት ያላስተዋልኩትን ነገር ስለነገረኝ
እየተገረምኩ
“አክረሜ ገና አንተ የሀያት እንደሆንክ ካወጅክ ጀምሮ
ደህና አይደለችም። ፈገግታዋ እና
ጨዋታዋ ሁሉ አንተን ደስ ለማሰኘት እንጂ የእዉነት
አይደለም። እየሳምኳት ራሱ
የምትጠራዉ ያንተን ስም ነዉ። ዛሬም ከምንም በላይ
ታፈቅርሀለች።” አለኝ።
በነገረኝ ነገር በጣም አዘንኩ። ግን ምን ማድረግ
እችላለሁ? እኔ አሁን ባለትዳር ነኝ።
“ምን ማድረግ የምችል ይመስልሀል?” አልኩት
እስክንድርን
“ቢያንስ ቀረብ ብለህ እንደድሮዉ አዉራት፣ አማክራት።”
አለኝ። እስክንድር ምን ያህል
ጉዳዩ እንዳሳሰበዉ ከፊቱ ይነበባል።
.
በነጋታዉ ክፍል ዉስጥ እየተማርን ሪቾ ራሷን ስታ
ወደቀች። የተቀመጠችዉ ከአጠገቤ
ስለነበር አቅፌ ከክፍሉ ይዣት ወጣሁ። እነሀያት ዉሀ
ገዝተዉ መጡና ሰዉነቷን
ለማቀዝቀዝ ሞከርን። ልክ እንደነቃች አይኗን ስትገልፅ
እቅፌ ዉስጥ ነች። ድክም ባለ
ፊቷ ላይ ፈገግታ ለመርጨት እየሞከረች “እዚህ እቅፍ
ዉስጥ እንኳ ብሞትም
አይቆጨኝም!” አለችኝ። ደግነቱ ሀዩ ሪቾ ስትነቃ
የምትበላዉ ነገር ልግዛ ብላ ሄዳ ነበር።
ከእቅፌ አዉጥቼ አስተካክዬ ላስቀምጣት ስል ገና
አካላቶቿ መታዘዝ አልጀመሩም።
እዛዉ እቅፌ ዉስጥ እንዳለች ማዉራት ጀመርን።
“መቼ ነዉ የጀመረሽ? ማለቴ ህመሙ?” አልኳት።
“ትንሽ ቆየ ባክህ! ጤናዬ አንተ ነበርክ ፤ የኔ እንደማትሆን
ካወቅኩ ጀምሮ ሰላም
አይደለሁም።” አለችኝ።
ያኔ ሽንፈቷን በፀጋ ተቀበለች ብዬ ተገርሜ ነበር። ለካ
በዉስጧ አፍናዉ ነበር።
.
የሴሚስተሩ ትምህርት እንዳለቀ ለክረምት ወደ አዲስ
አበባ ተመለስን። እህቴ መርየም
ኒካህ አድርጋለች። አሁን ሰርጉ ሊደገስ ነዉ። ከባህርዳር
እንደተመለስን ራሄል
በተደጋጋሚ ልታገኘኝ እንደምትፈልግ ብትነግረኝም ሀዩ
ሊከፋት ይችላል በሚል
ሳላገኛት ቀረሁ። እሁዱን የመርየም ሰርግ ሊካሄድ
ቅዳሜዉን ሴቶቹ እኛ ቤት
ተሰብስበዉ እየጨፈሩ ነዉ። እኔ ሰርግ ላይ ሴቶቹ
ሲጨፍሩ የሚሏቸዉ ግጥሞች
ስለሚያዝናኑኝ በቅርብ ርቀት ከሰዒድ ጋር ሆኜ እሰማለሁ።
አንድ የጎረቤታችን ልጅ
እያወጣች ሌሎቹ እየተቀበሉ እንዲህ አሉ
“ሽንኩርት ከተፍ ከተፍ ፣ ሽንኩርት ከተፍ ከተፍ፣
ያላገባ ካለ ፣ አሁን ይቀላጠፍ።” ሰዒድን እያየሁት
እስቃለሁ።
ኢስራዕ ማዉጣት ጀመረች፣ ሌሎቹ ይቀበላሉ
“በጎድጓዳ ሳህን፣ ይመታል አብሽ፣
የኔማ መርየሜ፣ የቀይ ድንቡሽቡሽ።
መስታወት ፊት እንጂ ፣ አያሳይም ሀገር፣
አደራ ጌታዬ ፣ የመርየምን ነገር።” አለችና ዛቻናልመና
የቀላቀሉ ግጥሞችን ማዉጣት
ጀመረች።
“መርየም ዘረ ብዙ ፣ መርየም ዘረ ብዙ፣
ትናገራትና ብዙ ነዉ መዘዙ።
አምናም አጨብጫቢ ፣ ዘንድሮም አጃቢ፣
ኧረ የኛን ነገር ፣ ያረቢ ያረቢ።”
.
ከሰዒዶ ጋር ግጥሞቹን ተመስጠን እያዳመጥን ሪቾ
ደወለች።
“ወዬ ሪቾዬ” አልኩ ስልኩን አንስቼ።
“አክረሜ እንዴት ነህልኝ?” አለች።
“የራሄል አምላክ ይመስገን ደህና ነኝ!” አልኳት እየሳቅኩ።
“አሁን ሰፈራችሁ ነኝ። አስፓልቱ ጋር ና ላግኝህ።”
አለችኝ።
ሄጄ አገኘኋት። የአባቷን መኪና ይዛ ነበር የመጣችዉ።
መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ ማዉራት
ጀመርን። ቆይ ግን ምድር ላይ የቀረሁት ወንድ እኔ ብቻ
ነኝ እንዴ? ይሄን የመሰለ ዉበት
ይዛ እኔን ደጅ መጥናቷ ጨነቀኝ። ሪቾኮ በጣም ዉብ ናት።
ድሮም ፎንቃ ይሉት ነገር
መዘዙ ብዙ ነዉ። ይኸዉ ሪቾን ራሱ አሳመመብኝ።
ሪቾ ብዙ የማላዉቃቸዉ በህይወቷ ዉስጥ ተፈጥረዉ
የነበሩ ነገሮችን ተረከችልኝ።
ከዛም አይን አይኔን እያየች “አክረሜ ሁሌም እወድሀለሁ
ግን ከዚህ በላይ መሰቃየት
አልችልም። ከዚህ በኋላም የማስቸግርህ አይመስለኝም።”
አለችኝ። እንባዋ ከአይኖቿ
ፈሰሰ። በጣም ልቤን ነካችዉ። እጆቼ እንባዋን ሊጠርጉ
ወደ ጉንጮቿ ሄዱ። ያዘቻቸዉ!
ሁለቱንም መዳፎቼን ሳመቻቸዉ። ልቤ ስፍስፍ ብሏል።
እጆቼን በኃይል ጎትታ ከንፈሮቼን
ወደ ከንፈሮቿ አስጠጋች። ልቤ ቀጥ አለ። የማስቆምበት
አቅም አልነበረኝም። ሁሉ
ነገሬን ተቆጣጥራዋለች። ወዲያዉ ስልኬ ጠራ። ተመስገን
ሙዷን አወረደዉ።
ለቀቀችኝና መሪዉ ላይ ተኛች። ሀዩ ነበረች የደወለችዉ።
አነሳሁት። ቤት እንደመጣች
እና ቶሎ እንድመጣ ነገረችኝ። ዛሬ ያዉ የባሏ እህት ሰርግ
ዋዜማም አይደል? ለሊቱን
ከእህቶቼ ጋር ሲጨፍሩ ሊያድሩ ነዉ።
ስልኩን አናግሬ ስጨርስ ራሄል ከመሪዉ ላይ ፊቷን አንስታ
በሶፍት እንባዋን
እየጠራረገች “በቃ ልሂድ!” አለችኝ። ትክዝ ብዬ አየኋትና
“አላህ ይጠብቅሽ!” አልኳት።
አትሄጂም ብዬ በሆነ ተዓምር ሚስቴ መሆኗን ባስረዳት
ደስ ይለኝ ነበር። ግን እዉነታዉ
ሪቾ ሚስቴ ያለመሆኗ ሀቅ ነዉ።
.
የሰርጉ ቀን አልፎ በማግስቱ ራሄል አራት ነጥብ በሚሴጅ
ላከችልኝ። ትርጉሙ
አልገባኝም ነበር። ስደዉልላት አታነሳም። በነጋታዉ ጠዋት
ሀያት ደወለችልኝ “አኩዬ የት
ነህ?” አለችኝ።
“ቤት ነኝ ሀዩዬ!” አልኳት።
“እሺ አልጋህ ላይ በወገብህ ተኛ አንዴ!” አለችኝ። ዛሬ
ደሞ ምን አይነት ሮማንስ ነዉ
ባካችሁ?
“አንቺ አዘሽኝ አይደለም አልጋ ላይ የጦር ጫፍ ላይ
አልተኛም ብለሽ ነዉ?” አልኩ
እንዳዘዘችኝ በወገቤ አልጋዉ ላይ እየተጋደምኩ።
“እሺ አኩዬ እንዳልኩህ ተኛህ?” አለችኝ።
“አዎ ሁቢ አሁን ምን ላድርግ?” አልኳት።
መጋደሜን እንዳረጋገጠች ድምጿ በሳግ እየታፈነ “አኩዬ
ሪቾ ራሷን አጠፋች!” አለችኝ።
እጄ ስልኬን መሸከም ከበደዉ። ስልኬ እንደዚህ ይከብድ
ነበር እንዴ? ራሄል የተገናኘን
ምሽት ላይ የነገረችኝ ነገር ስንብት መሆኑ ገባኝ። ሀዩ
አልጋ ላይ መሆኔን አረጋግጣ
የነገረችኝ ጉዳት እንዳይደርስብኝ በመስጋት ነበር።
እንደነገረችኝ የተኛሁ ቤት መጥታ
እስክታስነሳኝ ድረስ አልነቃሁም። አሁን ለቅሶ ስደርስ
አላፍርም? በኔ ምክንያት

ሞታ ሄጄ
ባለቅስ ማላገጥ አይመስልም? ሪቾዬ ጠልቻት እኮ
አይደለም። ግን ሁኔታዎች አንድ
ላይ እንዳንሆን አደረጉ። ሀይማኖታችን ተለያየ። ምን
ላድርግ? ምን ያህል ታፈቅረኝ
እንደነበር እኮ በደንብ ነበር የምረዳዉ። መላ አካሌን
የማዘዝ ስልጣን የነበረዉ ዉበት
እኮ ነበራት። ግን የፈጣሪ ዉሳኔ የሀዩ አደረገኝ። እነዛ ለዛ
ያላቸዉ ግጥሞቿስ? ወይኔ
ሪቾዬ! አሁን ማለቃቀሱ ምን ይጠቅማል? ምንም!!
.
በሀያት አስገዳጅነት የራሄልን ለቅሶ ለመድረስ ሄድን።
እስክንድር ቀድሞን ሄዶ ስለነበር
ስንደርስ ተቀበለን። በጣም እየተለቀሰ ነበር። ሀጅራ ለቅሶ
ልትደርስ ከኮምቦልቻ
እየመጣች ነዉ። ሪቾ በመርየም ሰርግ ቀን ራሷን
ያላጠፋችዉ ደስታዬን ላለማደብዘዝ
ብላ መሆኑ ገባኝ። እሷ እየተሰቃየች ለኔ ድርብ ደስታ
ትጨነቃለች። ለቅሶ ቤት ገብተን
ትንሽ እንደተቀመጥን የራሄል አባት ወደ ሀያት መጥተዉ
የሆነ ነገር አወሯት። ሀዩ ወደኔ
ጠቆመቻቸዉ። አባቷ ወደኔ መጡና “ና እስኪ አንዴ!”
ብለዉ ይዘዉኝ ወደ ዋናዉ ቤት
ገቡ። ወደ ራሄል መኝታ ቤት ስንገባ ራሄል ተገንዛ አልጋዉ
ላይ ተጋድማለች።
አልተከፈነችም። ከላይ አንሶላ ለብሳለች። አባትየዉ በሩን
ከዘጉት በኋላ አንሶላዉን
ከፊቷ ላይ አነሱት። ራሄል ሞታለች። ሳያት እንባዬ ከአይኔ
ያለማቋረጥ ፈሰሰ። ልቤ
በጣም ተነክቷል። አባትየዉ የሆነ የመድሀኒት ብልቃጥ
እየጠቆሙኝ “በዚህ ነዉ ራሷን
ያጠፋችዉ።” አሉኝ። የሰዉ ልጅ ጤዛ ነዉ። አሁን ታይቶ
በቅፅበት ዉስጥ የሚጠፋ።
ግን ምንም አይነት ፈተና ቢጋረጥ ነብስ ማጥፋት በፍፁም
እንደመፍትሄ ሊታይ
አይገባም። ምክንያቱም ከዚህ ከተኬደ በኋላ እዛ ሰማይ
ቤት የሚጠብቀንን ስቃይ
ካለንበት ችግር ጋር አወዳድረን አላየነዉምና!
.
ትንሽ የአልጋዉ ራስጌ ጋር ተቀምጬ ካነባሁ በኋላ
አባትየዉ አንድ ወረቀት ከኮታቸዉ
የዉስጥ ኪስ ዉስጥ አዉጥተዉ ሰጡኝ።
እዛዉ ከፍቼ አነበብኩት። የራሄል ፅሁፍ ነዉ።
“እንደምወድህ ከማዉቀዉ በላይ እንደምትወደኝም አዉቅ
ነበር። አንተን የኔ እንዳትሆን
ያገደህ ሀይማኖታችን መለያየቱ ብቻ ነዉ። ልክ ስታጣኝ
እዉነታዉን መጋፈጥ
ትጀምራለህ። ሁሌም ደስተኛ ሆነህ እንድትኖር
እመኝልሀለሁ። ግን ናፍቆትህን
አልችለዉምና ሞት እስኪያገናኘን ካላስቸገርኩህ ቢያንስ
በአመት አንድ ቀን መቃብሬ
አጠገብ እየመጣህ እንድታጫዉተኝ አደራ እልሀለሁ።
ተዉቤ እጠብቅሀለሁ።
አፈቅርሀለሁ።” ይላል።
.
ራሄል የፃፈችዉ ደብዳቤ ዉስጥ አንድም ሀሰት
አልነበረም። ግን ማነዉ ከሴቶች ጋር
ጓደኝነት መስርት ያለኝ? ሴትናወንድ መካከል ተፈጥሯዊ
መፈላለግ መኖሩ እንዴት
ጠፋኝ? ብሽቅ ነኝ።
ራሄልን እወዳት ነበር። ግን የወደፊት ህይወትን፣ ትዳርን
ሳስብ ሀይማኖታችን መለያየቱ
ትዝ አለኝ። እየወደድኳት አታዛልቀኝም በሚለዉ ሀያትን
መረጥኩ። እንጂ እኮ ራሄል
አጠገቤ ስትቆም በራሱ መላ ሰዉነቴን ነበር
የምትቆጣጠረዉ። እወዳት ነበር። የራሄልን
ደብዳቤ ጥብቅ አድርጌ ያዝኩት። በህይወት እያለሁ
ላልጥለዉ ለራሴ ቃል ገባሁ።
.
ይቀጥላል…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.