መንታ መንገድ ክፍል 12

መንታ መንገድ
ክፍል አስራሁለት
.
.
ራሄል የፃፈችልኝን ደብዳቤ ካነበብኩ በኋላ ከለቅሶ ቤት
አልጠፋሁም። ሀጅራ አዲስአበባ ደርሳ የራሄልን ሬሳ ስታይ
ራሷን መቆጣጠር ከበዳት። ለረዥም ሰዓት አነባች። ትናንት
ከጎኗ ትማር የነበረች ልጅ ሳይታሰብ መሞቷ ልቧን
ሰበረዉ። ሀጁ ወደ ኮምቦልቻ እስክትመለስ ድረስ ያለዉን
ጊዜ እነሀያት ቤት አሳለፈች።
ራሄል ዉጪ የነበሩት ዘመዶቿ እንደተሰበሰቡ በሞተች
በሶስተኛዉ ቀን ተቀበረች። ዉስጤ በሀዘን ተሞልቷል።
ገዳይዋ እንደሆንኩ እየተሰማኝ ነዉ። ራሄል ግን እወዳት
እንደነበር እንዴት አወቀች? አዎ ገባኝ ከሀያት በተለየ
ጊዜዬን ከሷ ጋር ነበር የማሳልፈዉ። አይኖቼ፣ ሁሉ ነገሬ
ከአንደበቴ ዉጪ እንደምወዳት ይናገር ነበር። ከፓፒረሱ
ክስተት በኋላ ግን የወደፊት ህይወትን ከግምት ዉስጥ
ባስገባ መልኩ ከራሄል እና ከሀያት ምርጫዬ መሆን
ያለባት ሀያት መሆኗን ወሰንኩ። ትኩረቴንም በከፊል
ከራሄል ወደ ሀያት አዞርኩ። ሀያት ምንም አይጎድላትም።
ግን ራሄል ልቤ ዉስጥ ነበረች።
.
በህይወት እስካለሁ ድረስ እንግዲህ ቢያንስ በአመት
አንድ ጊዜ ራሄል መቃብሯን እንድጎበኝ አደራ ብላኛለች።
ግን ሰዉ መንገድ ላይ ሲያየዉ ይሳሳለት የነበረዉ ዉበቷ
አፈር ገባ በቃ? ሰዉ ግን ከንቱ ነዉ። ምንም ዛሬ ቢፈካ
ላለመንጠፉ ዋስትና የለዉም።
.
ሀያት ሀዘኑ እንደከበደኝ ስለገባት በቻለችዉ አቅም ብቻዬን
አትተወኝም። በርግጥ ሰሞኑን አባዬ ትንሽ ስላመመዉ ስራ
እሱን ተክቼ መግባቴም ለጊዜዉም ቢሆን ሀዘኔን
እንድረሳዉ አድርጎኛል። ስራዉ ከአባዬ ድርጅት ጋር
መስራት የሚፈልጉ አዲስ ደንበኞች ሲመጡ ተቀብሎ
ማነጋገር፣ ወደብ ላይ ያሉ እቃዎችን በተመለከተ ከድርጅቱ
ሀላፊዎች ጋር በመመካከር ቶሎ እንዲገቡ ማድረግ ፣
ከሻጮች ጋር መደራደር ምናምን ነዉ። ብዙ ዉሳኔዎችን
በራሴ መወሰን ስለምፈራ አባዬ ጋር ደዉዬ እሱ እየነገረኝ
እኔ እፈፅማለሁ። ስራዉን ከዚህ በፊት አሳይቶኝ ስለነበር
ብዙም አልከበደኝም። የአባዬ ፀሀፊም ልምድ ስላላት
በደንብ ታግዘኛለች። ሀዩ ከስራ ስመለስ አብራኝ አምሽታ
ወደ ቤት ትሄዳለች።
ከራሄል አባት ጋርም በቅርብ እየተገናኘን እናወራለን።
እስክንድርንም በተደጋጋሚ አገኘዋለሁ። በራሄል ዙሪያ
የነበሩ ሰዎችን ሳወራ እሷን ያወራኋት ያህል ደስ ይለኛል።
እንዳለችዉም ሳጣት ከፍቅሯ እሳት ጋር መጋፈጥ
ጀምሬያለሁ። ትናፍቀኛለች። አንዳንዴ ሀያት ራሄልን
እንደነጠቀችኝ እየተሰማኝ ታስጠላኛለች። እንደዉም ሀዩ
ላይ በጣም ቀዝቅዤባት ነበር። ግን የሰዒዶ ምክር
አባነነኝ። “እሷም ራሷን አጥፍታልህ እንዳታርፈዉ!” ነበር
ያለኝ።
ቆይ አሁን ስለ ግጥም ከማን ጋር ነዉ የምወያየዉ?
ራሄልን በጣም እወዳት ነበር። ካጠገቤ ስትርቅ ሁሉም
ነገር ግልፅ ሆኖልኛል።
.
ቀናት ቀልድ አያዉቁም ፣ ወራትም ቀናት
ሲጠራቀሙላቸዉ እብስ ከማለት ወደኋላ አይሉም። ራሄል
ከሞተች ሁለት ወራት አለፉ። ክረምቱ አልቆ አዲስ አመት
ተበሰረ። ራሄል የሌለችበት ባዶ አመት አዲስ አመት ተባለ።
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲም በየቤታቸዉ የተበተኑ ተማሪዎችን
ጠራ። ከሀዩእና እስክንድር ጋር ሆነን ወደባህር ዳር ሄድን።
የመጨረሻ አመታችን ስለሆነ በዚህ አመት እንመረቃለን።
በአዉሮፕላን እየሄድን ሪቾ ትዝ ስትለኝ አጭር ግጥም
ፃፍኩ። ወደ መቃብሯ ስሄድ አነብላታለሁ።
“አንቺ የሌለሽበት ሁሉ ነገር ባዶ፣
ሰፈሩ ጭር አለ ፣በፅልመት ተጋርዶ።
ድምቀት ማለት አንቺ ፣ ስትጠፊ ገባኝ፣
ምንድነዉ ሳቃቸዉ ፣ ሰላም የሚነሳኝ?”
.
ሀያት በዉጤቷ አሁንም የክፍላችን ሰቃይ ናት። ሪቾ
ሞተች እንጂ ሁለተኛዉ ትልቁ ዉጤት የሷ ነበር። ድሮ
እኩል ነበርን። አሁን ግን በአንድ ትምህርት በልጣኛለች።
ግን ሞታለች። ትምህርት እንደተጀመረ እስክንድርን በጣም
ቀረብኩት። ራሄል ከናፈቀችኝ የማገኘዉ ብቸኛዉ ሰዉ
እስክንድር ነዉ። በርግጥ ጊዜዉ ሲገፋ የራሄል ሀዘንም
ቀለል ብሎልኛል። ሀያት ወደ ጣና እንደለመድነዉ ባጃጅ
ተኮናትረን ከሄድን ገና ፓፒረስ ጋር ከመድረሳችን በፊት
በወሬ ትጠምደኛለች። ወሬዉ ትኩረቴን ወደሷ ካልወሰደዉ
ከንፈሬ ላይ ትለጠፋለች። ፓፒረስን ካየሁ ራሄል ትዝ
ትለኛለች። ከራሄል ጋር ያሳለፍነዉን የፓፒረስን ምሽት
ሳስታዉስ ደግሞ ፈገግታ ይርቀኛል። የሀዩም ትኩረቴን
ለመስረቅ መሞከር ሪቾ ትዝ እንዳትለኝ ለማድረግ የታለመ
ነዉ። ቀናችንን ሰላማዊ ለማድረግ!
.
ትምህርት ተጀምሮ ከወር በላይ እንደተማርን አባዬ
በተደጋጋሚ መታመም ጀመረ። እኔናሀዩ አንዴ ወደ
አዲስአበባ መጥተን ጠይቀነዉ ተመልሰናል። እኛ
ስንጠይቀዉ ትንሽ ሰላም ነበር። ከተመለስን በኋላ ግን
ባሰበት።
ጠይቀነዉ በተመለስን በአስራአምስት ቀኑ የአባዬ ጤንነት
ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ኢስራዕ ነገረችኝ።
በየቀኑ እንደዋወላለን። በሰዓቱ እኔናሀዩ የመመረቂያ
ፅሁፋችንን ምዕራፍ አንድ ለማጠናቀቅ እየተጣደፍን የነበረ
መሆኑ አባዬን ደግሜ እንዳልጠይቀዉ አደረገኝ።
.
አንዳንዴ ማታ ከሀዩ ፣ ሀጁ እና እስክንድር ጋር ከተለያየን
በኋላ የግቢያችን ላቭ ስትሪት ላይ ብቻዬን ዎክ
አደርጋለሁ። እዚሁ መንገድ ላይ ሪቾ የፍቅር ግጥም
መፃፍ ጀመርኩ ብላ ስታነብልኝ የነበረዉ ድባብ ትዉስ
ይለኛል። እጆቿን ወደ ላይ ሰቅላ እየተሽከረከረች
ስትጨፍር አይኔ ላይ ድቅን ትላለች። ብቻዬን ስሆን ሀዘኑን
መቋቋም ይከብደኛል። ሪቾ በጣም ትናፍቀኛለች። ፓፒረስ
ዉስጥ ራቁታችንን ሆነን ከንፈሬን ስትስመኝ
የማልቆጣጠረዉ ስሜት በጥፊ እንድመታት እንዳደረገኝ
አስታዉስና ይገርመኛል! እስከአሁን መልስ ያጣሁለት
ጥያቄ! አካሌን ማን አዘዘዉ? ልቤ እኮ ሙሉ ለሙሉ
ሊተኛት ፈልጎ ነበር።
.
ሀሙስ ጠዋት ላይ ኢስራዕ ደወለችልኝ። “ወዬ የኔ
ሚጢጢ!” አልኳት።
“አቢ እኮ ወደ አኼራ ሄደ!” አለችኝ እያለቀሰች። አኼራ
ማለት ቀጣዩ አለም ማለት ነዉ። አባቴ ሞተ? እንባዬ
ፈሰሰ! ሲያመጣዉ እንግዲህ አንዴ ነዉ። አባቴን በጣም
ነበር የምወደዉ። ከተረጋጋሁ በኋላ ለሀዩ ደዉዬ ነገርኳት።
ሀዩ በጣም አዘነች። ሀዘኑ በጣም እንዳይጎዳኝ ፈርታለች።
እኔ ግን በልኩ ነዉ ያዘንኩት። አባቴ በመሞቱ ጌታዬን
አላማርርም። እድሜዉ ሄዷል። ከሀዩ ጋር አራት ሰዓት ላይ
ቢዝነስ ፍላይት አግኝተን ወደ አዲስአበባ መጣን። ሰዒድ
ከአየርማረፊያ ተቀብሎን የኛ ቤት ቅያስ ጋር ካደረሰን
በኋላ እናቱን ለማምጣት እኛን ወደ ሰፈር የሚያስገባዉ
ቅያስ ጋር አዉርዶን ሄደ። ወደ ቤት እየቀረብን ስንመጣ
አንድ ሰዉዬ ፈገግ ብሎ እዚህ ሰፈር ከሆንን ለቅሶ ቤቱን
እንድናሳየዉ ጠየቀን። እሺ ብለነዉ አብረን መሄድ
እንደጀመርን ሰዉየዉ እየቀለደ ሊያስቀን ሞከረ። ያወቀኝ
አልመሰለኝም። ለቅሶ ለመድረስ የመጣዉ ግን እኛዉ ጋር
ነበር። ልክ ቤት ጋር ስንደርስ በራችን ላይ የተደኮኑትን
ድንኳኖች እያሳየሁ “እዛ ቤት ነዉ!” አልኩት። ወዲያዉ
ማጓራት እና እየጮኸ ማልቀስ ጀመረ። እየጮኸ እኛን
ትቶን ወደ ድንኳኑ እየፈጠነ ሄደ። እዉነት ለመናገር ሳቄን
ልለቀዉ ምንም አልቀረኝም። ሰዉ እንዴት ድንኳን ሲያይ
ይቀየራል? ማስመሰል ምን ያደርጋል? ሀዘኑን ለመግለፅ
እንደከብት ማጓራት አይጠበቅበትም እኮ! አስመሳይ!
.
ቤት እንደገባሁ ኢስራዕናመርየም አቅፈዉኝ መንሰቅሰቅ
ጀመሩ። ሳያቸዉ አንጀቴን በሉት ከአይኔ እንባዬ ፈሰሰ።
ወዲያዉ እነሱን አረጋግቼ የአባቴ ሬሳ ወዳለበት ክፍል
ገባሁ። አባዬ ተከፍኖ በጣም ደስ የሚል ሽቶ ተቀብቷል።
ያን የመሰለ መኪና እንደማይዝናሱፍ እንዳልቀያየረ ዛሬ
በአቡጀዴ ተጠቀለለ። ግንባሩን ስሜዉ ወዲያዉ ወደ
ድንኳን ሄድኩ። ሰው እየጮኸ ያለቅሳል። ሀይማኖታችን
ከማንባት
በዘለለ እየጮኹ

ማልቀስን ስለሚከለክል ሰዎቹ ዝም
እንዲሉ ለመጠየቅ ሞከርኩ ግን ሊሰሙኝ አልቻሉም። ኋላ
ላይ አንድ ሽማግሌ ተቆጥተዉ ወንዶቹን ስርዓት
አስያዙልን። ድንኳን ዉስጥ እንደተቀመጥኩ አንድ
ጎረቤታችን ጠርታ ወደ ሴቶች ድንኳን ይዛኝ ሄደች።
በእስልምና እምነት መሰረት በሰርግም ሆነ በለቅሶ
ወንዶች ከሴቶች ጋር እንዲቀላቀሉ አይፈቀድም። የሴቶች
ድንኳን ጋር ስደርስ ሴትየዋ “ኧረ እናትህን ተይ በላት ፊቷን
ቧጣ ጨረሰችዉ። አላህም አይወደዉ!” አሉኝ። ወደ
ሴቶች ድንኳን ስመለከት እናቴ ደረቷን እየደበደበች ፊቷን
እየቧጠጠች ታለቅሳለች። ከአባዬ ሬሳ አርቀዉ ድንኳን
ዉስጥ ያስገቧት በጣም አስቸግራ መሆኑ ገባኝ። አባቴ
በህይወቱ በነበረበት ጊዜ ስታቆስለዉ ኖራ ዛሬ
ታስመስላለች። እናቴ ሆና ክብሯ ባይዘኝ ባጋጫት ሁላ ደስ
ይለኝ ነበር። ወይ የሀይማኖት እዉቀት የላት! ወይ ስነ
ምግባር የላት፣ መልክ ብቻ!
እናቴ መምጣቴን ስታይ ትንሽ ተረጋጋች። እንዲሁ ለኔ
ክብር አላት። እህቶቼን ከቤት ጠርቼ ስርዓት እንዲያስይዟት
ነገርኳቸዉ።
.
አባዬ ወዲያዉ ሰባት ሰዓት ላይ ተሰግዶበት ተቀበረ።
በእስልምና እምነት በሬሳ ላይ የሚሰገድ የስግደት አይነት
አለ። ሬሳን ቶሎ መቅበርም ይወደዳል።
በነጋታዉ ሰው ሀዘኑ እየበረደለት ድንኳኑ ዉስጥ መጫወት
ጀመረ። ግማሹ አስፈርሾ ይቅማል። ግማሹ ክብ ሰርቶ
ይጫወታል። ጮክ ብሎ ሚስቅ ሁሉ ነበር። አሪፍ
የቤተሰብ መሰብሰቢያ መድረክ ሆኗል። ለቅሶ መሆኑን
ረሱት መሰለኝ።
ማታዉን ቤተሰብ ተሰብስቦ የአባዬን ስራ ማን ያስተዳድር
በሚለዉ ላይ መከረ። መጨረሻ ላይ እኔ ላይ እምነታቸዉን
ጥለዉ ትምህርቴን አቋርጬ የአባቴን ስራ እንድሰራ
ወሰኑ።
.
ለቅሶዉ ቀዝቅዞ ፣ ድንኳኑ ፈራርሶ ፣ሰው እንደተበተነ ፤
ሀዩንም ወደ ባህርዳር ሸኘኋት። ቢያንስ እስኪ ሰቃያችን
ትመረቅ። እኔና ሪቾ እንደሆነ ከትምህርት መስመር
ወጥተናል። ትንሽ ቆይቼ እኔም ወደ ባህርዳር ሄጄ
ልብሶቼን ይዤና ዊዝድሮዉ ሞልቼ ተመለስኩ። የህይወት
መስመር መቼ እንደሚቀየር አይታወቅም። ትናንት ተማሪ
የነበርኩት ልጅ ይኸዉ ሰራተኛ ልሆን ነዉ።
.
ስራ በጀመርኩበት የመጀመሪያዉ ቀን ማታ የሪቾን መቃብር
ሄጄ ጎበኘሁ። ወደ ባህርዳር ስበር የፃፍኩትን ግጥም
አነበብኩላት። ሪቾ እንዳለችዉ የእዉነትም ተዉባ
እየጠበቀችኝ ይመስለኛል። እንዲህ ሱፍ ለብሼ የአባቴን
መኪና ይዤ ሪቾ ብታየኝ ምን ትል ነበር? እኔንጃ ብቻ ለየት
ያለ ቃል አታጣም። የሆነ ነገር ትለኝ ነበር።
.
የአባዬን ስራ እያስተዳደርኩ ቀናትም እየሮጡ ወራትም
እየተገነጠሉ ሰባት ወራት አለፉና የሀዩ እና ሀጅራ ምርቃት
ደረሰ። የፈጣሪ ዉሳኔ ነጠለን እንጂ እኔናሪቾም አብረን
እንመረቅ ነበር።
በነገራችን ላይ የአባዬን ስራ በጣም ትርፋማ
አድርጌዋለሁ። በቅርቡ እንደዉም ባለን ተቀማጭ ገንዘብ
ሌላ ተጨማሪ ስራ ለማስጀመር እያሰብኩ ነዉ።
.
ቅዳሜዉን ዉዷ ሚስቴን ላስመርቅ ወደ ባህርዳር ሄድኩ።
ሀዩዬ የግቢዉን ትልቁን ዉጤት ነበር ያስመዘገበችዉ።
አራት ነጥብ! በጣም አኮራችኝ። ሀዩ ግን ከመመረቋ
በላይ ጓግታለት የነበረዉ አብረን የምንኖርበት ቀን
መድረሱን ነዉ። በሰርግ ከቤቷ በወጉ የምትወሰድበትን
ቀን! የምንጠቃለልበትን እለት!
ሀዩን ሜዳሊያ አጥልቃና ዋንጫ ይዛ ሳያት በጣም ደስ
አለኝ። ሪቾ ከኛ ጋር ባለመሆኗ ግን አዘንኩ።
ሀዩ ፍልቅልቅ እንዳለች ዙሪያዋን የቆሙትን ቤተሰቦቿን
እና እኔን እያየች “የሀያትን ምርቃት ከሌሎች ምርቃቶች
ለየት የሚያደርገዉ በሰርጓ ዋዜማ መካሄዱ ነዉ።” አለች።
.
ይቀጥላል…

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.