መንታ መንገድ ክፍል 15 የመጨረሻው ክፍል

እናመሰግናለን።
መንታ መንገድ
ክፍል አስራአምስት

.
.
ሀዩዬ እንደሷ ቆንጆ ልጅ ወልዳልኝ ሆስፒታል ከተኛች
በኋላ በሀኪሞቹ ፈቃድ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ወሰድናት።
እናቷ ሁሉንም ነገር አዘጋጅተዉ ጨርሰዉ ነበር። ገንፎ
ለሀዩ ይሰራል መግፊ በሷ እያሳበበች ትበላለች።
የኔናየመግፊ የሰሞኑ ትርርባችን በገንፎዉ ጉዳይ ላይ
ነዉ። ፓምፐርስ ምናምን ከመግፊ ጋር ሆነን ገዝተናል።
መግፊ ሆነ ብላ ሴሪፋም አስገዝታ መሳቂያ አደረገችኝ።
ለካ እስከ ስድስት ወር ከጡት ሌላ ምንም አይነት ምግብ
ለህፃናት አይሰጥም።
ሀዩዬን ልጃችንን ስታጠባ አየኋት ፤ የሆነ ልብ የሚይዝ
ነገር አለዉ። ልጇን ስትንከባከብ በጣም ደስ ትላለች።
.
በሰባተኛዉ ቀን ሁለት በግ አርደን ሰደቃ አወጣን። ሰደቃ
ማለት ምፅዋት ማለት ነዉ። በሀይማኖታችን መሰረት ልጅ
በተወለደ በሰባተኛዉ ቀን የሚደረገዉ ይህ የምፅዋት
ዝግጅት አቂቃ ይባላል። በነገራችን ላይ ለልጃችን ስም
ለማዉጣት በጣም ብዙ ክርክር ነበር የተፈጠረዉ።
መጀመሪያ ራሄል እንድትባል ፈልጌ ነበር። ግን የሀዩም
የኔም ቤተሰቦች በራስ ላይ ሀዘንን ማባባስ አያስፈልግም
ብለዉ ተቆጡኝና ተዉኩት። እንደዉም የሀዩ እናት
“ለሀያትም ስሜት አስብ እንጂ! ማትፈልጋት
እንዳይመስላት!” ነበር ያሉኝ። ሀዩ ብዙ ነገር ስላደረገችልኝ
ስሜቷን መጠበቅ ይኖርብኛል። ራሄልን ለመዘከር ሆቴሉ
ይበቃል። ብዙ የስም ምርጫዎች ከቀረቡ በኋላ መጨረሻ
ላይ “ራህማ” የሚለዉ የኔ ምርጫ ተቀባይነት አገኘ። እኔ
ራህማ እንድትባል የፈለግኩት ከራሄል ሞት በኋላ
የነበርኩበትን መጥፎ ሁኔታ ፣ አልጋ ላይ የነበረብኝን
ያለመረጋጋት ችግር እና ጥፊዬን ችላ ለኖረችዉ ዉዷ
ሚስቴ ሀያት ስጦታ እንዲሆን በማሰብ ነዉ። ነብዩ አዩብ
(እዮብ) በሽታ ሲፈራረቅበት ፣ ሀብቱ ሁሉ ሲወድም እና
ሌሎች ሚስቶቹ ትተዉት ሲሄዱ በፅናት ከጎኑ የቆየችዉ
አንዷ ሚስቱ ራህማ ብቻ ነበረች። እናም የኔ ልጅ ከብዙ
ችግር በኋላ የተገኘች ናትና የሚስቴን ትዕግስት ለመዘከር
ራህማ አልኳት። ራህማ ማለት እዝነት ማለት ነዉ።
.
ሀጅራ ፣ እስክንድር እና የሪቾ ቤተሰቦች ፤ ቤት መጥተዉ
ሀዩን አራስ ጠይቀዋታል። በነገራችን ላይ ሀጅራ
ታጭታለች። በቅርቡ ማግባቷ አይቀርም። የአክስቴ ልጅ
እና የዉዱ ጓደኛዬ ሰዒድ ሚስት ኢማን ሰሞኑን ከነሀያት
ቤተሰቦች ቤት ጠፍታ አታዉቅም። ኢስራዕ እና መርየም
ቤታቸዉ አድርገዉታል። ከመግፊራ ጋር ሆነዉ ሀዩን
ያዳብሯታል። እናቴም ከአባቴ ሞት በኋላ ትንሽ ስርዓት
ይዛለች። ከአክስቶቼም ጋር ታርቀዋል። ምግብ እየሰራች
ለሀዩ ይዛላት ትመጣለች። ከምር ልጅ ግን የደስታ ምንጭ
ነዉ። ስራ ዉዬ ማታ አይኗን እስከማይ እንዴት እንደምጓጓ!
በርግጥ ለሀዩዬ ያለኝም ፍቅር በጣም ጨምሯል።
.
ጊዜዉ በሀዩ ፍቅርና በራህማ ጨዋታ ታጅቦ ነጎደ።
ራህማዬ ሁለት አመት ሞላት። የራሄል ሆቴል ግንባታም
ተጠናቀቀ። አጠቃላይ እቃዎቹን ሳይጨምር ለግንባታ ብቻ
አስር ሚሊየን ብር አዉጥተናል። በርግጥ ቢዝነሱ
አስተማማኝ ስለሆነ በአመት ዉስጥ ይመልሰዋል። በዛ
ላይ ሀዩን የመሰለች የምርጥ ጭንቅላት ባለቤት ናት
የምታስተዳድረዉ። የዉስጥ እቃዎቹን ከዉጭ
ካስመጣንናእነሀያት ሰራተኞችን ከቀጠሩ በኋላ
የሚመረቅበት ቀን ደረሰ። ሆቴሉ በአክሲዮን የተከፈተ
ነዉ። የእኔ ቤተሰብ ፣ የሀያት ቤተሰብ ፣ የራሄል ቤተሰቦች
፣ እስክንድር ፣ ሰዒድ እና ሀጅራ ነን ባለድርሻዎቹ። ትልቁ
ድርሻ ግን የኔ እና የሀዩ ቤተሰቦች ነዉ። የሆቴሉ የቦርድ
ሰብሳቢ እኔ እንድሆን ተወስኗል። ሆቴሉን በስራ
አስኪያጅነት ደግሞ ሀያት ትመራዋለች። ምክትል ስራ
አስኪያጁ ልምድ ያለዉ ሰዉ ነዉ። ሀጅራ እና እስክንድርም
ዉስጥ ላይ የሀላፊነት ቦታዎችን ይዘዉ ይመራሉ።
ከምርቃቱ በፊት የማስታወቂያ ክፍላችን ሆቴላችን
በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እንዲተዋወቅ አደረገ። እነሀያት
በስራዉ በጣም ተወጥረዋል። እኔ እንኳ የራሴን ስራ
ስለምሰራ በሳምንት አንዴ ነዉ ሪፖርታቸዉን ለማዳመጥ
የምሄደዉ።
.
ጠዋት ቢሮ ስገባ ፀሀፊዬ ሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ስላሉ
እቃዎች ካወራችኝ በኋላ አንድ ደብዳቤ ሰጥታኝ ወጣች።
ከራሄል ሆቴል ይላል። እነሀያት እንደላኩት ገመትኩ። ከፍቼ
አነበብኩት።
“የራሄል ሆቴል የምርቃት ስነ ስርዓት በቀጣዩ ሳምንት
እንደሚደረግ ይታወቃል። በመሆኑም ሆቴሉ የራሄል
መታሰቢያ እንደመሆኑ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ስለ ራሄል
የሚዳስስ አጭር ፅሁፍ መቅረብ ይኖርበታል። ስለሆነም
እንደ ሆቴሉ የቦርድ ሰብሳቢነትዎ በእለቱ ይህን ሀሳብ
ባካተተ መልኩ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉልን
በአክብሮት እንጠይቃለን። ከሰላምታ ጋር!” ይላል። ከስሩ
የሀያት ፊርማ አለዉ። ረዥም ሰዓት ብቻዬን ሳቅኩ። ለምን
ሳቅኩ? ሀዩ ለኔ ደብዳቤ መፃፏ ገርሞኝ! እሷ ስራ ላይ
ቀልድ አታዉቅም።
.
የሆቴሉ ምርቃት ሲጠጋ ሀያት ስራ ስለበዛባት አንዳንዴ
አስፈቅዳኝ እዛዉ ታድራለች። ራህማን ሁሌም ስራ ስትሄድ
ይዛት ነዉ የምትሄደዉ። “አንተ እኔን እንጂ እሷን ማቀፍ
አትችልበትም!” ትላለች ሀዩ። ለነገሩ ራህማ መራመድ እና
ትንሽ ትንሽ መናገር ጀምራለች።
ከብዙ ዉጥረት በኋላ የራሄል ሆቴል ምርቃት ደረሰ። የዛን
ቀን ሀዩ ሆቴል ስለነበር ያደረችዉ ከኢስራዕናማማ ጋር
ሄድኩ። መርየም ከባሏ ጋር ሄዳለች። የሆቴላችን በር ላይ
ስደርስ ድባቡ ለየት ያለ ነዉ። መኪናዬን የሆቴሉ ፓርኪንግ
ጋር አቁመን ወደ ዉስጥ ገባን። ሱፍ የለበሱ ወጣቶች
ወዲያዉ እየተቀላጠፉ ወደ ሆቴሉ አዳራሽ ይዘዉን ሄዱ።
ብዙ ሰዉ አለ። አዳራሹ ጋር ስንደርስ ሀዩ በሩ ጋር ቆማ
እንግዳ እየተቀበለች አገኘኋት። ሰላም ካለችን በኋላ
ኮሌታዬን አስተካክላልኝ ወደ ተዘጋጀልን መቀመጫ
ወሰደችን። እንግዳዉ ሁሉ ቦታ ቦታ ከያዘ በኋላ መድረክ
መሪዉ ወደ መድረክ ወጥቶ የእለቱን ዝግጅቶች
አስተዋወቀ። ከዚያም ሀያትን ወደ መድረክ ጠርቶ እኔን
ንግግር እንዳደርግ እንድትጋብዘኝ አደረገ። እንግዲህ
የቦርድ ሰብሳቢዉ በስራአስኪያጇ መጋበዙ ነዉ። ሀዩ
ስታወራ አንቱ እያለችኝ ነበር። እኔ ሳቄን ለመቆጣጠር
እየታገልኩ ነዉ።
.
መድረኩ ላይ ወጥቼ ንግግሬን ጀመርኩ። ሁሉም አፉን
ከፍቶ ያዳምጣል።
“ዛሬ በዋናነት በስራ አስፈፃሚዎቻችን ብርታት ሆቴላችንን
ለመመረቅ በቅተናል። ግን መረሳት የሌለበት፤ ሆቴሉ
ትናንት አብራን በአንድ ጎዳና ላይ ስትጓዝ የነበረችናብዙ
ህልም የነበራት ጓደኛችን መታሰቢያ መሆኑ ነዉ። የራሄል
ዉበት በሆቴላችን አይነግቡነት ይገለፃል። የሰላ ብዕሯን
የማስታወቂያ ቡድናችን ተቋማችንን ያስተዋዉቅበታል።
ለሰዉ የነበራትን ፍቅር ሰራተኞቻችን እርስ በእርስ
ይዋደዱበታል። እሷን መልሰን ማግኘት ባንችልም ሆቴሉን
ትልቅ ደረጃ በማድረስ ከፍ አድርገን እንዘክራታለን። ራሄል
ሆቴል በይፋ ተከፍቷል!!” አልኩና ከመድረኩ ወረድኩ።
ታዳሚዉ ያጨበጭባል።
.
የመንግስት ባለስልጣናት ዲስኩራቸዉን ካሰሙ በኋላ
ታዳሚዉ ሆቴሉን እንዲጎበኘዉ ተደረገ። በየኮሪደሩ ላይ
የራሄል ፎቶ በሚያምር ፍሬም ተሰቅሏል። አንድ ጥግ ላይ
ደግሞ የራሄል የተመረጡ ግጥሞች በልዩ ዲዛይን
ተሰርተዉ ግድግዳዉ ላይ ተሰቅለዋል። አይኔ አንዱ
ግጥም ላይ አረፈ። መንታ መንገድ ይላል አርዕስቱ
“መንታ መንገድ ፊት ቆሞ ፈራጁ፣
ምረጥ ተባለ ከመንገዶቹ፣
ግራዉን መንገድ እየወደደዉ
ለሀይማኖት ሲል ቀኙን መረጠዉ።
ቀኝ በጎ ነዉ ሲባል የሰማ፣
ነገዉን ብሎ ግራዉን ያማ፣
ሚስኪን አፍቃሪ ፍቅሩን ተቀማ።
ግራዉ ፈራጁን ማግኘት ቢነፈግ፣
ፈገግታ ሰጡት ለቅሶ ሚሸሽግ።
ሳቀ ሳቀና አንብቶ አንብቶ፣
ፈራጅን ሲያልም ዉሎ አምሽቶ፣
ተስፋ ሲቆርጥ ፣ ፈርሶ አደረ፣
ከተጠራበት ፣ ከህ

ይወት ቀረ።”
ይሄ ግጥም ራሄል ተስፋዋ ሙጥጥ ሲልናራሷን ልታጠፋ
በወሰነችበት ቅፅበት የፃፈችዉ እንደሆነ ገመትኩ። “ምን
ያህል እንደምወድሽ ብታዉቂ!” አልኩ በልቤ! ግን ህይወት
የእዉነታ እንጂ የስሌት ጉዳይ አይደለችምና እዉነቱን
ማስተናገዱ ይሻላል።
ስለዚህ ነገር አልተነገረኝም ነበር። የሪቾን ግጥሞች በዚህ
መልኩ ሳያቸዉ እንድደመም አስባ ይሆናል ሀዩ
ያልነገረችኝ። የራሄል ቤተሰቦች ባዩት ነገር በጣም
ተደምመዋል። ምን እነሱ ብቻ እኔ ራሱ የሌለ
ተደንቄያለሁ። ሌላዉ በጣም የሚገርመዉ ራሄል ለእኔ
የፃፈችዉ የስንብት ደብዳቤ በትልቁ ግድግዳዉ ላይ
የተፃፈበት ልዩ የመመገቢያ ክፍል መኖሩ ነዉ። ስገምት
ሴቶች ባላቸዉን ለመጋበዝ የሚመርጡት ሁነኛ ቦታ
የሚሆን ይመስለኛል። ስታጣኝ እዉነቱን ትጋፈጣለህ
አይነት ማስፈራሪያ ሲፈልጉ ማለት ነዉ።
በሀዩ የአመራር ብቃት ተደመምኩ። በቀጣይ ደግሞ ሆቴሉ
የአስጎብኚ ቡድን እንዲኖረዉ ለማድረግ አቅደዋል። ሀዩ
ታቅዳለች እኔ እየሳቅኩ እፈርማለሁ።
.
ጉብኝቱን ጨርሰን ምግብ ልንበላ የምግብ አዳራሹ ዉስጥ
ስንገባ ሰዒዶናኢማን ይዘዉኝ ያደረግከዉ ንግግር
የፖለቲከኛ ይመስላል ብለዉ ፎገሩኝ። ሰኢዶናኢማን አንድ
ወንድ ልጅ ወልደዋል። ሙሀባ ብለዉታል። የራሄል አባት
በተሰራዉ ስራ የተሰማቸዉን ደስታ ገለፁልኝ። ወዲያዉ
አንድ የራሄል ቤተሰብ የሆነ ልጅ መጥቶ አድናቆቱን
ከገለፀልኝና በዚህ እድሜዬ እንደዚህ ለስኬት መብቃቴ
እንደገረመዉ ነግሮኝ ጥያቄ አዘነበብኝ። እሱ ሀብቴ
ብዙዉን የዉርስ መሆኑን አያዉቅም። ሲቀጥል ሆቴሉን
በዚህ መልኩ የማስተዳድረዉ እኔ መስየዋለሁ። ሀዩ
እንደሆነች አያዉቅም።
“አንድ ቆንጆ ምክር እስኪ ምከረኝ!” አለኝ ከኔናከሀዩ ጋር
እየተቀመጠ
“በወንድናበሴት መካከል ተፈጥሯዊ መፈላለግ አለ።
ስለዚህ ሴት ልጅ ሚስትህ እንጂ የልብ ጓደኛህ አትሁን!”
አልኩት። ሀያት ሳቋን ለቀቀችዉ። እኔ ጓደኞቼ ሴቶች
በመሆናቸዉ የገባሁበትን ጭንቅ እኔ ነኝ የማዉቀዉ።
ራሄል ጓደኝነት በቀደደዉ መንገድ ፍቅር ላይ ወድቃ ነዉ
እስከሞት የደረሰችዉ።
“አንተ ጓደኛህን አይደል እንዴ ያገባኸዉ?” አለኝ ወደ ሀያት
እየጠቆመ
“አዎ ግን የሞተችዉም ጓደኛዬ ናት።” አልኩትና ወደ ሀዩ
እየጠቆምኩ “እሷም ብትሆን ደስታዬ የሆነችዉ ከተጋባን
በኋላ ነዉ።” አልኩት።
ልጁ ፈገግ ብሎ ልጃችንን እና ከኛ ቀጥሎ ያለዉ ጠረጴዛ
ላይ የተቀመጡትን ቤተሰቦቻችንን እያየ ሳቀና “የናንተ
ቤተሰብ በጣም ያስቀናል!” ብሎን እየሳቀ ከመቀመጫዉ
ተነስቶ ወደ ቤተሰቦቻችን ጠረጴዛ ሄደ። የልጁ ድፍረት
ገረመኝ። ራሄል በወንዱ ነገር ነዉ። ከእናቴ ጋር ማዉራት
ጀመረ። ስቀን ዞር አልን።
.
ከሁለት ቀን በኋላ እኔ መኝታ ክፍል ዉስጥ ጋደም
ብያለሁ። ሀዩ ራህማን ስታጫዉት ይሰማኛል። የምትለዉን
ራህማ እንድትደግመዉ እያደረገች ትስቃለች።
“ረበና” አለች ሀዩ
“አፐና” ትላለች ራህማ! ሀዩ በሳቅ ፍርስ ትላለች
“ማ ኸለቅተ ሀዛ”
“ማተዛ” ትላለች ራህማ! አሁን እኔም በጣም መሳቅ
ጀምሬያለሁ። ሀዩ በጣም እያዝናናት ነዉ መሰለኝ
ቀጠለች።
“ባጢለን ሱብሀነክ!”
“ባክነን” አለች ራህሚ! በሷ ቤት ሀዩ ያለችዉን መድገሟ
ነዉ። አንደበቷ ይጣፍጣል። ከምር ግን እንደ ልጅ ምንም
የሚያስደስት ነገር የለም። ሀያት ራህማን ስታስብላት
የነበረዉ የቁርዓን አንቀፅ ነዉ። “ረበና ማ ኸለቅተ ሀዛ
ባጢለን ሱብሀነክ!” ነበር ያለችዉ። ትርጉሙ “ጌታችን
ሆይ ይህን (ድንቅ አለም) እንዲሁ (ያለ ዓላማ)
አልፈጠርከዉም …” ማለት ነዉ። ፈጣሪ ምድርና ሰማይን
እንዲህ ያስዋበዉ የስዕል ጥበቡን ለማሳየት አይሆንም።
ስለዚህ በከንቱ ያልተፈጠረ ምድር ላይ ከንቱ መሆን
አይገባም። ምድር በከንቱ አልተፈጠረችም። እኛም
ለጨዋታ አልተፈጠርንም። ህይወታችን ቁምነገር ሊሆን
ይገባል!! “የራሄል አምላክ እዉነት ተናገረ!” አልኩ አልጋዉ
ላይ እንደተዘረርኩ። አልረሳት ነገር ከልቤ ታትማ ፤ የኔ
አትሆን ነገር ከመቃብር ከትማ! ጌታዬን ራህማን እና
ሀያትን ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ። የተከለከልናቸዉ
ከሚመስሉን ነገሮች ይልቅ የተሰጡን ዋጋ አላቸዉ።
.
ተፈፀመ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.