ዘለፋ ዛቻ ጥላቻ የትም አያደርሰንም

አቧራው ሲረግብ መንገዱ ይጠራል!

በማንም ሰው ላይ ጥላቻ የለኝም። በቀላሉ የምገፋም ሰው አይደለሁም። አሸዋ ላይ አልቆምኩም! ዘለፋ፣ ፍረጃ፣ ጥላቻ፣ ዛቻ… ትክክል ነው ብዬ ባላምንም ተጠራጣሪነት የፈጠረው ስጋት በተለያየ መልኩ እየተገለጠ እንደሆነ ነው የምረዳው። ዛሬ ለውጡን የሚመራው አካል ከኦሮሞ የወጣ ቡድን ባይሆን ራሱ እንዲሁ በጥርጣሬ እየታያየን ብዙ መባባላችን አይቀርም ነበር። እያንዳንዷን ድርጊት እንደፀጉር እየሰነጠቅን መወጋገዛችን ከአሁኑ አይለይም ነበር። የትናንቱ ጦስ ስነልቦናችን ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል። ያለፈው ጠባሳ ያልሻረለት በርካታ ኢትዮጵያዊ ዛሬም ትከሻውንን እያየ ተሳቆ ቢሄድ፤ ሁሉ ሁሉን ቢጠራጠር ገራሚ አይሆንም!

ይህ እንደማህበረሰብ ያጋጠመን ችግር ነው። ያለፉት ገዢዎቻችን በተለያየ መልክ ገዝግዘው ያጠፉት አንዱ እሴት መተማመንን ነው። ሁላችንም የዚህ ሰለባ ሆነናል። እኔ የምደክመው ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ይህ የለውጥ ዕድል ዳግም ከጃችን እንዳይወጣ ነው። ፍፁም ነኝ ብዬ አላምንም – ብዙ ልሳሳት እችላለሁ – ሰው ነኝ። ሁሉንም በእኩል ለምታቅፍ ኢትዮጵያ ይበጃል የምለውን ከማድረግ ግን ቅንጣት አልሰስትም። አዲሲቷን ኢትዮጵያ እናፍቃለሁና። በሰው ልጅም ተስፋ አልቆርጥም – የማይለወጥ የለምና። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደመሃል ይመጣል። ሊበራሊዝም ይለመልማል!

ይህን አቋም የሚጋሩኝን በስልጣን ላይ ያሉም የሌሉም ሀይሎች እንዲሳካላቸው መመኘት ብቻ ሳይሆን አቅሜ በፈቀደ ሁሉ እደግፋቸዋለሁ። ወጀቡ ሲያልፍ በጠራው ሰማይ በውቡ ባህር ልጆቻችን ይቦርቃሉ – አቦራው ሲረግብ በጠራው መንገድ በህብረት ለሰው ልጅ እድገት በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ! እንዲህ እንዲህ እያልን ዛሬ በፍቅር እና በተስፋ የምንፈጥረው ነገ ብሩህ ይሆናል! ወዳጄ ይኸው ነው!

ሁላችሁም ክቡር የሰው ልጅ ናችሁ – ፍቅር ለሰው ሁሉ!

✌ Yonathan tr

አርተፊሻል ድምበር

ይህ የምታዩት የቤልጂየምና የኔዘርላንድ ድንበር ነው! ከመስመሮቹ ወደዚህ ቤልጂየም ከመስመሮቸቹ ወደዛ ደግሞ ኔዘርላንድ! ወታደር የለም! ታንክ የለም! መትረየስ የለም!

የሰው ልጅ እንዲህ ሰልጥኖ ድንበሩን በነጭ ቀለም ብቻ በሚያሰምርበት በዚህ ዘመን አንተ እገሌ ከክለሌ ይውጣልኝ እያልክ ከገዛ ወንድምህ ጋር በገጀራ ስትከታከት ትውላለህ! ዓለም ጥሎህ ሄዷል ወዳጄ!!!
በ Dagmawi Dagmawi

ከአሁን በውኀላ አህዳዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አይመለስም

የኦሮሞ ህዝብ ሀገራችን ለደረሰችበት የለዉጥ እና የተስፋ ምዕራፍ ከወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን መራራ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍሏል፡፡

የህዝባችን ዋና ዋና የትግል አጀንዳዎች ነጻነት እንዲሰፍን፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የግል እና የቡድን መብቶች እዲከበሩ፣ ዜጎች ላይ የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ፣ የተደራጀ ሌብነት እንዲቆም፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሰፍን…ወዘተ የሚሉ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድም ቀን ፌዴራሊዚም ስርዓቱን ተቃርኖ ቆሞ አያውቅም፡፡ ፓርቲያችን ኦዲፒም ይህን ጉዳይ በተመለከተ በሁለት ጽንፎች የሚቀነቀኑ የመገንጠልም ሆነ አሀዳዊ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የኦሮሞን ህዝብ ህዝብ የማይጠቅሙ ከመሆናቸውም በላይ የሀገራችንን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እና ወደፊት የማያራምዱ ናቸዉ ብሎ ያምናል፡፡ ሰለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በከፈው መስዋእትነት እየተገነባ ያለዉ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት እንዲጎለብት ጠንክሮ ይሰራል፡፡

የህዝባችንን የትግል አጀንዳዎች ከግብ በማድረስ ሁሉም በእኩልነት፣ በነጻነት እና በወንድማማችነት የሚኖርባት ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ኦዲፒ ከሌሎች ዴሞክራቲክ ሃይሎች ጋር በመትጋት ላይ ይገኛል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መብትና ጥቅሞች ህብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በማጠናከር፣ እውነተኛ ዴሞክራሲን በማስፈን፣ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በሰለጠነ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይከበራል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በጽናት በመታገላችንን እንቀጥላለን!

አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ