ሀያላን የሰውን ልጅ አዕምሮ በረቀቀ መንገድ መቆጣጠር እንዴት ቻሉ?

በማህበረሰብ ስነልቦና ፍቺ Indoctrination ሀሳብ፣ አመለካከትና ረቂቅ የሆነውን የአስተሳሰብ ስልት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የማስረጊያ መንገድ ነው፡፡ Indoctrination ለሰው ልጆች ተፈጥሮኣዊ በሆነው ዕውነትን የመረዳት አካባቢን የማወቅና አመለካከት የመያዝ ሂደት/ socialization / እጅግ የተለየና አብዛኛውን ጊዜም አሉታዊ አንድምታ ያለው ቃል ነው፡፡

Indoctrination እና ትምህርትን የሚለያያቸው ነገር Indoctrinated የተደረገ ግለሰብ የመጠየቅና እንዲያውቅ የተደረገውን ዕውነት የመፈተሽ ዝንባሌ አይኖረውም፣ ተምህርት በአንፃሩ ጠያቂና በብርቱ የሚፈትሽ አዕምሮን ያጎናፅፋል፡፡
Indoctrination ለፓለቲካ ፍጆታ ሲውል ሃይልን በእጁ ያደረገ ተቋም ይበጀኛል፣የስልጣን ዘመንን ያራዝምልኛል የሚለውን የተቀበሸበ እውነት/ Manipulated truth / በት/ት ስርዓት በስነፅሁፍ፣ ኪነጥበብ፣ በማስሚዲያ፣ በህዝብ ማዘውተሪያ፣ ወዘተ በማስረፅ የግለሰቦችን አመለካከት በተፈበረከ ዕውነት ለማሳት ይጠቀሙበታል፡፡

በሃገራችን ትምህርት ዕውቀትን ከማዳረስና ድንቁርናን ከማጥፋት ይልቅ የህዝቦችን አዕምሮ በመቆጣጠር ጥቂት አካላት የሚኖራቸውን የግል ፍላጎት እንደ ዕውነታ እንዲወሳ በየትምህርት ስርዓቱ በመካተቱ ዜጎች የቱንም ያህል ለዕውቀት ቢተጉም ትምህርት የሰው ልጆችን አዕምሮ የሚለውጠውን ያህል ሳይቀይራቸው ቀርቶ በኣሳፋሪ ግብር፣በወረደ ምግባር ሲዘፈቁ ተስተውለዋል፡፡ ይህ የሆነው ሃራችን ውስጥ ትምህርት በገዢው መደብ በመጨቆኑ በየት/ቤቱና ተቋማት ውስጥ ዜጎች የታቀደላቸውን ዕውነት ሲጋቱ ዘመናትን ባጁ እንጂ አሳቢ፣ጠያቂ፣ ምክኒያታዊ፣ስሜቱን እንዲገዛ የሚያደርገው ት/ት ተነፍጓቸው ከርመዋል፡፡ በላቀ ትምህርትና ሁለንተናዊ በሆነ እውቀት ያላለፈ፣ Indoctrinate የተደረገ ማህበረሰብ:

• ስለተነገረው ዕውነት ጠልቆ ማሰብ አይደፍርም
• ራሱንና ሰውኛ ልዕልናውን በመጠርጠር የበታችነት ስሜት ያሳያል
• መረጃን በማጣራት፣ወደ ዕወቀት በማሳደግ ጥበብን ወደ ውስጡ የማስረግ ብቃት የለውም
• Indoctrinate ላደረገው አካል “humble robot” ነው፡፡ ነፃ ፈቃዱ በሙሉ በጥቂቶች ቀጥጥር ስር ነው፣ እጅግ አስገራሚው ነገር የሚቆጣጠረውን አካል አለማወቁና ማወቅ አለመፈለጉ ጭምር ነው፡፡
• የዚህ አይነት ግለሰቦች ጠንካራ የሆነ የመነዳት ስሜት/strong conformity/ ሲያሳዩ ውስጣዊ ብቃታቸውን በእጅጉ ስለሚጠረጥሩ ከፊታቸው ለሚገኝ አካል አጎብዳጅ /obedient / ናቸው፡፡

በዚህ የተነሳ አዕምሯቸው ራሱን በራሱ /self imprisoned/ ስለከረቸመ ዕምቅ ችሎታቸውን ሳይመረምሩ ነፃ አውጪ ፍለጋ ይማትራሉ፣ ባርነቱ ረቂቅ እና አዕምሯዊ በመሆኑ የመላቀቂያ ሂደቱ ቀላል አይሆንም፡፡ አሁን ላይ እየሆነብን ያለውም ይሄው ነው! ትምህርትን እንሻ፣ የተሰጠንን ዕውቀት እንመርምር፡፡

እውነትን ታውቃላችሁ፣ እውነቱም ነፃ ያወጣችኋል !
“and you shall know the truth, the truth shall set you free”

Advertisements

ልጅ እያለሁ እጅግ አራስወዳድ ነበርኩ

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ
“የአባቴ ሦስቱ ምክሮች”

የወቅቱ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንግ ፒንግ ጥሩ ስትራቴጂ አዋቂና የሀገር መሪ ብቻ አይደሉም፡፡ ጥሩ ወግ አዋቂ ጭምር እንጂ፡፡ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ስለልጅነት ጊዜያቸው ተናገረዋል፡፡
“ልጅ እያለሁ፣ እጅግ በጣም ራስ ወዳድና ሁሉንም ነገር ለኔ ባይ ነበርኩኝ” ይላሉ ፕሬዝዳንተ ሺ ጨዋታቸውን ሲጀምሩ፡፡ ለግማሽ ክፍለዘመን ወደኋላ በትዝታ እያሰቡ ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡
ራስ ወዳድ ከመሆኔ የተነሳ ሁል ጊዜም ጥሩ ጥሩውን ለራሴ ነበር የምወስደው፡፡ ይህ ባህሪዬ ቀስ በቀስ ጓደኛ እያሳጣኝ መጣ፡፡ በመጨረሻም ጓደኞቼ ሁሉ ሸሽተውኝ ጓደኛ አልባ ሆንኩ፡፡ እኔ ግን ጥፋቴ ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ጓደኞቼ ስለሸሹኝ ኮነንኳቸው እንጂ ጥፋቴ ምን እንደሆነ ራሴን አልጠየኩም፡፡ ቢሆንም፣ አባቴ ሕይወትን በመልካም መንገድ እንዴት መምራት እንደምችል በተግባር አስተማረኝ፡፡
የአባቴ የሕይወት ትምህርት ሶስት ደረጃዎች ነበሩት፡፡
አንድ ቀን አባቴ፣ ለሁለታችን የሚሆን ምግብ አዘጋጀና በሁለት ሳህን ከፍሎ የምግብ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠው፡፡ ምግቡ ፓስታ (ኑድል) በእንቁላል ነበር፡፡ አባቴ ፓስታውን ሲያስቀምጠው በአንደኛው ሳህን ከፓስታው በተጨማሪ የተቀቀለ አንድ እንቁላል ከአናቱ አድርጎበታል፡፡ በሌላኛው ሳህን ግን ከፓስታው በላይ እንቁላል የለም፡፡ ከዚያ አባቴ ወደ እኔ እየተመለከተ፣ “ልጄ የትኛውን ትፈልጋለህ? አንዱን ሳህን ምረጥ” አለኝ፡፡
በጊዜው፣ እንቁላል እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ ምግብ አይደለም፡፡ አዲስ ዓመት ካልመጣ ወይም ዓመትባል ካልደረሰ በቀር እንቁላል መብላት ዘበት ነው፡፡ ፈጥኜ እንቁላል ያለበትን ሳህን መረጥኩ፡፡ በሰዓቱ፣ ሳህኑን ሳነሳ ቅንጣት ታህል አላመነታሁም፡፡ ደስ እያለኝ መብላት ጀመርኩ፡፡
አባቴ ሁለተኛውን ሳህን አንስቶ መመገብ ሲጀምር አይኔን አላመንኩም፡፡ አባቴ ከሚበላበት ሳህን ውስጥ ሁለት የተቀቀሉ እንቁላሎች በፓስታው ተሸፍነው ኖሯል፡፡ ተቆጨሁ በጣም! ቸኩዬ በመወሰኔ ራሴን ወቀስኩት፡፡
ይሄን ጊዜ አባቴ እየሳቀ፣ “የኔ ልጅ፣ አይኖችህ የሚያዩት ሁሉ እውነት እንዳልሆነ መቼም እንዳትረሳ! በሰዎች ላይ ብልጣብልጥ ለመሆን ስትሞክር ትጎዳለህ!!” አለኝ፡፡
በሌላ ቀን፣ አባቴ በተመሳሳይ ምግብ አዘጋጅቶ ሲያበቃ እንደተለመደው ፓስታውን በሁለት ሳህን አቀረበው፡፡ አንደኛው ሳህን አናት ላይ አንድ የተቀቀለ እንቁላል አስቀምጦበታል፡፡ በሌላኛው ግን ከላይ ምንም እንቁላል አላደረገበትም፡፡ ከዚያ እንደተለመደው አባቴ ወደ ምግብ ጠረጴዛው እየጠቆመ “ልጄ፣ ምረጥና የምትፈልገውን ሳህን ውሰድ” አለኝ፡፡
ካለፈው ስህተቴ በመማር በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብኝ አሰብኩና ቀልጠፍ ብዬ ከአናቱ እንቁላል የተደረገበትን ትቼ ሌላኛውን መረጥኩ፡፡ ከዚያ በፍጥነት ፓስታውን ገላለጥኩና ሳህኑን አየሁት፡፡ በጣም ደነገጥኩ! ሳህኑ ውስጥ አንድም እንቁላል የሚባል ነገር የለም፡፡
አባቴ በድጋሚ እየሳቀ፣ “ልጄ፣ ሁል ጊዜ በልምድህ ላይ ብቻ የምትተማመን ከሆነ ትከስራለህ፡፡ አንዳንዴ ሕይወት ራሷ ልታሞኝህ ወይም ቁማር ልትጫወትብህ ትችላለች፡፡ ዳሩ ግን፣ በዚህ ብዙ ልታዝን ወይም ልትቆጣ አይገባም፤ ትምህርት እንደሚሆንህ ቆጥረህ እለፈው፡፡ እንዲህ ያለውን እውቀት ከመማሪያ መፅሀፍት ላታገኝ እንደምትችል አስታውስ” ብሎኝ፣ ያ ቀን አለፈ፡፡
ለሶስተኛ ጊዜ አባቴ ምግብ አዘጋጀ፡፡ እንደተለመደው ፓስታ እና እንቁላል በሁለት ሳህኖች ቀርበዋል፡፡ በአንዱ ሳህን የተቀቀለው እንቁላል ከፓስታው በላይ ተቀምጧል፡፡ በሌላኛው ሳህን ደግሞ ፓስታ ብቻ…፡፡ የውስጡን አላውቅም፣ ከላይ ግን እንቁላል የለም፡፡ አባቴ የተለመደው ጥያቄውን አቀረበልኝ፡፡ ወደ ምግብ ጠረጴዛው እየጠቆመ፣ “ልጄ ምረጥ! የትኛው ሳህን ይሁንልህ?” አለኝ።
አሁን እኔ ከሁለት ሥህተቶቼ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡
“አባቴ አንተ የቤቱ አባወራ ነህ! ለቤተሰባችን ሰርክ የምትለፋ አባት ነህ፡፡ መጀመሪያ መብላት ያለብህ አንተ ነህ፤ ይገባሃልም፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ አንተ አንሳ…” ስል መለስኩለት፡፡
አባቴ በጭራሽ አላቅማማም…፡፡ ከአናቱ እንቁላል የተቀመጠበትን ሳህን አንስቶ መብላት ጀመረ፡፡ እኔም ሁለተኛውን አንስቼ ፓስታዬን ለመብላት አቀረቀርኩ፡፡ እርግጠኛ ነበርኩ፣ ሳህኑ ውስጥ እንቁላል እንደማይኖር፡፡ ከፓስታው በታች ሁለት እንቁላሎችን ሳገኝ ግን አይኔን ማመን አልቻልኩም፡፡
ቀና ብዬ ሳየው፣ አባቴ ፈገግ ብሎ በፍቅር አይኑ እያስተዋለኝ ነበር፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል መከረኝ፤ “የኔ ውድ ልጅ! ለሌሎች ሰዎች መልካም መልካሙን ስታደርግ ተፈጥሮ ራሷ መልካም መልካሙን ወደ አንተ ታመጣለች! ይሄንን መቼም እንዳትዘነጋ” አለኝ፡፡
ከዚያን ጊዜ በፊትም ሆነ፣ ከዚያን ጊዜ በኋላ አባቴ ብዙ ጊዜ መክሮኛል… ገስፆኛል፡፡ አብዛኞቹን ማስታወሴን እጠራጠራለሁ፡፡ ነገር ግን፣ እነዚህ ሦስት ምክሮቹን በፍፁም አልረሳቸውም… እስክሞት ድረስ፡፡ እነሆ ሕይወቴም በዚህ ምክንያት የተስተካከለ ሆኗል፡፡ ከአባቴ ምክር በኋላ ስኬት መንገዷን ወደ እኔ አድርጋለች፡፡
አባቱን የሚወድ ሼር
ምንጭ: Long Live Ethiopia

ዘለፋ ዛቻ ጥላቻ የትም አያደርሰንም

አቧራው ሲረግብ መንገዱ ይጠራል!

በማንም ሰው ላይ ጥላቻ የለኝም። በቀላሉ የምገፋም ሰው አይደለሁም። አሸዋ ላይ አልቆምኩም! ዘለፋ፣ ፍረጃ፣ ጥላቻ፣ ዛቻ… ትክክል ነው ብዬ ባላምንም ተጠራጣሪነት የፈጠረው ስጋት በተለያየ መልኩ እየተገለጠ እንደሆነ ነው የምረዳው። ዛሬ ለውጡን የሚመራው አካል ከኦሮሞ የወጣ ቡድን ባይሆን ራሱ እንዲሁ በጥርጣሬ እየታያየን ብዙ መባባላችን አይቀርም ነበር። እያንዳንዷን ድርጊት እንደፀጉር እየሰነጠቅን መወጋገዛችን ከአሁኑ አይለይም ነበር። የትናንቱ ጦስ ስነልቦናችን ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል። ያለፈው ጠባሳ ያልሻረለት በርካታ ኢትዮጵያዊ ዛሬም ትከሻውንን እያየ ተሳቆ ቢሄድ፤ ሁሉ ሁሉን ቢጠራጠር ገራሚ አይሆንም!

ይህ እንደማህበረሰብ ያጋጠመን ችግር ነው። ያለፉት ገዢዎቻችን በተለያየ መልክ ገዝግዘው ያጠፉት አንዱ እሴት መተማመንን ነው። ሁላችንም የዚህ ሰለባ ሆነናል። እኔ የምደክመው ልክ እንዳለፉት ጊዜያት ይህ የለውጥ ዕድል ዳግም ከጃችን እንዳይወጣ ነው። ፍፁም ነኝ ብዬ አላምንም – ብዙ ልሳሳት እችላለሁ – ሰው ነኝ። ሁሉንም በእኩል ለምታቅፍ ኢትዮጵያ ይበጃል የምለውን ከማድረግ ግን ቅንጣት አልሰስትም። አዲሲቷን ኢትዮጵያ እናፍቃለሁና። በሰው ልጅም ተስፋ አልቆርጥም – የማይለወጥ የለምና። የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደመሃል ይመጣል። ሊበራሊዝም ይለመልማል!

ይህን አቋም የሚጋሩኝን በስልጣን ላይ ያሉም የሌሉም ሀይሎች እንዲሳካላቸው መመኘት ብቻ ሳይሆን አቅሜ በፈቀደ ሁሉ እደግፋቸዋለሁ። ወጀቡ ሲያልፍ በጠራው ሰማይ በውቡ ባህር ልጆቻችን ይቦርቃሉ – አቦራው ሲረግብ በጠራው መንገድ በህብረት ለሰው ልጅ እድገት በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ! እንዲህ እንዲህ እያልን ዛሬ በፍቅር እና በተስፋ የምንፈጥረው ነገ ብሩህ ይሆናል! ወዳጄ ይኸው ነው!

ሁላችሁም ክቡር የሰው ልጅ ናችሁ – ፍቅር ለሰው ሁሉ!

✌ Yonathan tr